ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ነገ አዲስ አበባ ይገባሉ

የኤርትራው  ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በኢትዮጵያ ጉብኝት ለማድረግ  በነገው ዕለት  አዲስ አበባ ይገባሉ  ፡፡

በኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር  አብይ አህመድ ግብዣ መሰረት በነገው ዕለት ወደ አዲስ አበባ  የሚገባው በፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የተመራ የኤርትራ  ከፍተኛ የልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ  የሁለት ቀናት ጉብኝት እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በኢትዮጵያ ቆይታቸው  የሁለቱ አገሮችን ታሪካዊ ወዳጅነት ለማጠናከር በቅርብ የተጀመረው ጥረት በሚጠናክርበት ሁኔታ ላይ  ከዶክተር አብይ አህመድና ከአገሪቱ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች ጋር ምክክር እንደሚያደርጉ ተገልጿል ፡፡

ዶክተር አብይ አህመድ በአስመራ ጉብኝታቸው ወቅት ከኤርትራ ፕሬዚደንት ጋር የፈረሙትን የሰላምና የወዳጅነት ስምምነት የጋራ መግለጫ የሚያከብርና የሚያወድስ ፕሮግራም የሚካሄድ ይሆናል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ለተመራው የልዑካን ቡድን ኤርትራውያን ወንድሞችና እህቶች በአሥመራ ደማቅ አቀባበል ያደረጉ ሲሆን የኤርትራ የልዑካን ቡድን ነገ  አዲስ አበባ ከሚገባት ጊዜ ጀምሮ የተለየ የወዳጅነት መስተንግዶ ለማድረግ በመንግስት አስፈላጊው ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ ተመልክቷል፡፡ 

በፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ለሚመራው ወንድም ለሆነው የኤርትራ የልዑካን ቡድን እንግዳ ተቀባዩ  የኢትዮጵያ ህዝብ ደማቅ አቀባበል እንዲያደርግ ተጋብዟል፡፡

የኤርትራ  ልዑካን  ቡድን ጉብኝት በሁለቱ አገሮችና ህዝቦች መካከል የተጀመረውን ጠንካራና ሁለንተናዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የተወሰደ መልካም እርምጃ ነው ተብሏል፡፡

በኢትዮጵያና ኤርትራ መሀከል የተደረሰውን አዲስ የሰላም እርምጃ ተከትሎ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሚቀጥለው ሳምንት ከ20ዓመት በኋላ የመጀመሪያውን በረራውን ያደርጋል፡፡(ምንጭ: የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈትቤት )