በኢትዮጵያ የአርጀንቲና አምባሳደር ጉስታቮ ግሪፖ በጠቅላይ ሚኒስትሩ መሪነት በሃገሪቱ እየመጣ ያለውን ለውጥ አደነቁ።

በኢትዮጵያ የአርጀንቲና አምባሳደር ጉስታቮ ግሪፖ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መሪነት በኢትዮጵያ እየመጣ ያለውን ለውጥ አደነቁ።

አምባሳደሩ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ ጋር የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት በሚያጠናክሩበት ሁኔታ ላይ መክረዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለዋልታ ቴሌቪዥን በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው አምባሳደሩ በዶክተር አብይ አህመድ መሪነት በኢትዮጵያ እየተካሄዱ ያሉትን የለውጥ እንቅስቃሴዎች አድንቀዋል።

አምባሳደሩ በተጨማሪም የአርጀንቲና ፕሬዝዳንት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የላኩትንም መልዕክት አድርሰዋል።

አርጀንቲና በሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን ዘርፎች ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር ለማሳደግ ቁርጠኛ መሆኗንም ነው የተናገሩት አምባሳደሩ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ በበኩላቸው በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ትብብር የበለጠ ማስፋት ያስፈልጋል ብለዋል።