ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን ለመቀበል ዝግጅት ማድረጉን መንግስት ገለፀ

በኢትዮጵያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት የሚያደርጉትን የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን ለመቀበል  መንግሥት በቂ ዝግጅት ማድረጉን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሚያደርጉትን ጉብኝትን በተመለከተ  የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚንስትር አቶ አህመድ ሽዴ በዛሬው ዕለት መግለጫ ሠጥተዋል።

አቶ አህመድ በመግለጫቸው እንደገለጹት በፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሚመራ የኤርትራ ልዑክ በኢትዮጵያ የሶስት ቀናት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ለማድረግነገው ዕለት አዲስ አበባ የሚገቡ በመሆኑ በፀጥታና ደህንነት  ረገድ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅቶች ተጠናቀዋል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ባለፈው ሳምንት ኤርትራ አስመራ አውሮፕላን ጣቢያ በተደረገላቸው ደማቅ አቀባበልለፕሬዚዳንት ኢሳያስም በአዲስ አበባ አለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ መደገም አለበትብለዋል ኃላፊ ሚንስትሩ።   

ህብረተሰቡ በነገው ዕለት  ለሚገባው የኤርትራ ልዑካን ቡድንም አቀባበል ሲያደርግ የሁለቱን አገሮች ህዝቦች አብሮነት በሚያጎለብትና ሰላማዊ በሆነ መንገድ መሆን እንዳለበት ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።

በፕሬዚዳንት ኢሳያስ የሚመራው የኤርትራው ልኡክ ከአዲስ አበባ ቆይታው በተጨማሪም የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ እንደሚጎበኝም ኃላፊ ሚንስትሩ አስታውቀዋል።

የፊታችን እሁድ እለትም በሚሊንየም አዳራሽ 25 ሺህ ህዝብ የሚገኝበትየኢትዮጵያ እና የኤርትራ ሰላም ማብሰሪያመድረክ ይካሄዳል ብለዋል።   

በሚሊኒየም  አዳራሽ  በሚካሄደው መድረክም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ተገኝተው ለሁለቱም ህዝቦች አብሮነትና አንድነት ንግግር ያደረጋሉ ብለዋል።

በመድረኩ የኢትዮጵያ  የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችም የሁለቱን ሀገራት ሰላም፣ አንድነትና ፍቅር  የሚያንፀባርቁ የተለያዩ ስራዎችን በመድረኩ ላይ እንደሚያቀርቡ ተገልጿል።

በመጨረሻም ህብረተሰቡም የፀጥታው እና የሰላሙ ዋና ባለቤት ከመሆኑ አንጻር ከአቀባበሉ ጋር  በተያያዘ የተለየ ነገር በሚመለከትበት ጊዜ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በመተባበር የአቀባበል ስነ ሥርዓቱ ሰላማዊ እንዲሆን ሚንሰትሩ የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።