ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የመራው የኤርትራ ልዑካን ቡድን አዲስ አበባ ገብቷል

የልዑካን ቡድኑ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርስ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፣ የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች እንዲሁም የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦች ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ወደ አዲስ አበባ የመጡት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ግብዣ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

ፕሬዝዳንቱ በኢትዮጵያ በሚኖራቸው የሶስት ቀናት ቆይታ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና ከሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ እንደሚወያዩም ይጠበቃል።

በፕሬዝዳንት ኢሳያስ የሚመራው የኤርትራው ልዑክ በአዲስ አበባ ከሚያደርገው ቆይታ በተጨማሪም የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክን ይጎበኛል፡፡

በነገው ዕለትም በሚሊንየም አዳራሽ 25 ሺህ ህዝብ የሚገኝበት “የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ሰላም ማብሰሪያ” መድረክ ይካሄዳል፡፡

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ እንዳሉት፣ በኢትዮጵያ ያለው የኤርትራ ኤምባሲ የማደስ ሥራው ተጠናቆ ይፋዊ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ይከናወናል፡፡