ህብረተሰቡ ግጭት ማስነሳት ለሚሹ አካላት ተባባሪ እንዳይሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ ጠየቁ

ህብረተሰቡ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ግጭት ለማስነሳት ለሚፈልጉ አካላት ተባባሪ እንዳይሆን  ጠቅላይ  ሚንስትር ዶክተር አብይ ጠየቁ ።

ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ በዛሬው ዕለት በአገሪቱ  ጉብኝት  ሲያደርጉ የነበሩትን የኤርትራው  ፕሬዚዳንትን በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ደማቅ አሸኛኘት አድርገውላቸዋል ።

ከሽኝቱ  በኋላ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ  በሠጡት መግለጫ  እንደገለጹት  የአዲስ አበባና አካባቢዋ ነዋሪዎች እንዲሁም የሐዋሳ ነዋሪዎች ለፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ላደረጉት ደማቅ  አቀባበልም ታላቅ ምስጋና አቅርበዋል ።  

ጠቅላይ ሚንስትሩ በመግለጫቸው  ህብረተሰቡ  በአንዳንድ  አካባቢዎች ግጭትና አለመረጋጋት  እንዲከሰት  ለሚፈልጉ አካላት  ትብብር እንዳያደርግም  ጥሪ አድርገዋል ።

በአገሪቱ  አንዳንድ አካባቢዎች እየተከሰቱ የሚገኙት ግጭቶች  ከተጀመሩት የፍቅርና የመደመር  ጉዞ ጋር አብረው  የማይሄዱ   በመሆናቸውም በአፋጣኝ  መቆም  እንዳለባቸው ጠቅላይ  ሚንስትሩ  አጽዕኖት ሠጥተው ተናግረዋል ።

በሶማሌና አሮሚያ አካባቢዎች ግጭቱ  የቀጠለ መሆኑን  በመጠቆም  በርካታ ንጹሐን ሰዎች እየሞቱ ነው ፣ ግጭቱን  ለጊዜው ማስቆም  ባይቻል እንኳን   ህብረተሰቡ በሁኔታው  ተባባሪ  ባለመሆን  ተገቢውን ጥንቃቄ  እንዲያደርግ  ጠይቀዋል ።

የአዲስ አበባ ፖሊስና የፌደራል ፖሊስ ግጭት ሊያስነሱ የሚችሉ አካላትን  በመቆጣጣር ረገድም   ተገቢውን  ሥራ እያከናወነም   እንደሚገኝም  ጠቅላይ ሚንስትሩ  በመግለጫቸው አመልክተዋል ።

ከውጭ  ምንዛሪ ጋር  በተያያዘ  በግል  የውጭ  ገንዘቦችን  ይዘው  የሚገኙ  ሰዎች   ወደ ባንክ  ሄደው  እንዲመነዝሩ  ጥሪ ያቀረቡት  ጠቅላይ ሚንስትሩ   መንግሥት  በሂደት  በሚወስደው እርምጃ  ጉዳት  እንዳይደርስባቸው  ከወዲሁ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው ተናግረዋል ።