ኮሚሽኑ ህብረተሰቡና የፀጥታ ሃይሉ የፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጉብኝት በሰላም እንዲጠናቀቅ ላደረጉት አስተዋጽኦ ምስጋና አቀረበ

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጉብኝት በሰላም እንዲጠናቀቅ ህብረተሰቡና የፀጥታ ሃይሉ ላደረገው አስተዋጽኦ ምስጋናውን አቀረበ።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘይኑ ጀማል፥ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የፕሬዚዳንቱ ጉብኝት በሰላም እንዲጠናቀቅ የሚጠበቅበትን መወጣቱን ተናግረዋል።

በተለይም የአዲስ አበባ፣ የሃሳዋና ሻሸመኔ አካባቢ ወጣቶች ለሰላሙ ዘብ በመሆን ምንም አይነት የፀጥታ ችግር እንዳይፈጠር ያደረጉት አስተዋጽኦ የሚያኮራ ነው ብለዋል።

የሃገር መከላከያ ሠራዊትን ጨምሮ የፌደራል ፖሊስና ሌሎች የፀጥታ መዋቅር አካላትም፥ በቅንጅት የሠሩት ሥራ የፕሬዚዳንቱ ጉብኝት በሰላም ለመጠናቀቁ መሠረት መሆኑንም ነው የተናገሩት።

አሁን የታየውን የፀጥታ ኃይሉና የህብረተሰቡ በጋራ ሰላም የማስጠበቅ ሂደት አጠናክሮ በማስቀጠል የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ ይገባልም ብለዋል።

የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በኢትዮጵያ ያደረጉትን የሶስት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት አጠናቀው ዛሬ ወደ ሃገራቸው መመለሳቸው ይታወሳል።(ኤፍቢሲ)