የአሰብ ወደብን ለመጠቀም የሚያስችል እንቅስቃሴ በፍጥነት ተጀምሯል- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

የአሰብ ወደብን በቶሎ ለመጠቀም የሚያስችል እንቅስቃሴ በሁለቱም ሃገራት መጀመሩን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር  አስታውቋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም እንደገለጹት  የአሰብ ወደብ አገልግሎት በአፋጣኝ የሚጀምሩበት ሁኔታ እንዲመቻች የሁለቱ ሀገራት መሪዎች መመሪያ ሰጥተዋል፡፡

ከትራንስፖርት ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ማሪታይም አገልግሎት ባለስልጣን፣ ከኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክ አገልግሎት ድርጅት እንዲሁም ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ አካላት ያሉበት ግብረ ሀይል ተቋቁሞ ዝግጅት እየተደረገ ነውም ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ በኩል ወደ አሰብ የሚወስደው መንገድ የጥገና ስራ እንደተጀመረ የገለጹት አቶ መለስ በኤርትራም በኩል ተመሳሳይ ስራ ተጀምሯል ብለዋል፡፡

አቶ መለስ አክለውም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አስመራ የሚያደርገውን መደበኛ በረራም በነገው እለት በይፋ እንደሚጀምር ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የትኬት ቢሮውን በአስመራ ከፍቷል ያሉት አቶ መለስ፥ በቀጣይም የበረራ ቁጥሮቹን ከፍ እያደረገ እንደሚሄድ አስታውቀዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኤርትራ አየር ክልልን በመጠቀሙ በአማካኝ ያጣው የነበረውን 100 ሺህ ዶላር ያስቀርለታል ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኤርትራ አየር መንገድን 20 በመቶ ድርሻ እንደሚኖረውም አቶ መለስ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በነገው እለት በሚጀምረው በረራም 465 ሰዎች ወደ አስመራ ይጓዛሉ እንደሚጓዙም ታውቋል፡፡

ከእነዚህም ውስጥ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ ባለሀብቶች እና ለዓመታት ከቤተሰቦቻቸው ተለያይተው የቆዩ ኤርትራውያን ይገኙበታል ነው ያሉት።

ምቹ የአየር ግንኙነት መፈጠሩ ኢንቨስተሮችን ለመሳብ እና የቱሪስቶችን ፍሰት ለመጨመር እንደሚረዳም በመግለጫው ተወስቷል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ወደ ሃላፊነት  በመጡ ማግስት ያለ ምንም ይሉኝታ ለአገራችን፣ ለሁለቱም አገራትና ለአካባቢው ይጠቅማል ብለው የወሰኑት ውሳኔ ፍሬ ማፍራቱን ያሳያል ብሏል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በመግለጫው፡፡