አየር መንገዱ ወደ አስመራ የሚያደርገውን በረራ በይፋ ጀመረ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አስመራ የሚያደርገውን በረራ ዛሬ በይፋ ጀምሯል።

የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማሪያም በዚሁ ስነ ስርዓት እንደተናገሩት የበረራው መጀመር ላለፉት 20 ዓመታት ተቋርጦ የነበረውን ግንኙነት በአዲስ ምዕራፍ የሚያስተሳስርና የሚያጠናክር ነው።

አየር መንገዱ አስመራን ከአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ዓለማት ጋር የሚያስተሳስርና ለአፍሪካ ኩራት መሆኑን ያስመሰከረበት ነውም ብለዋል።

አየር መንገዱ ዛሬ በይፋ ወደ አስመራ በረራ የሚያደርግ ሲሆን ከተለያየ የማህበረሰብ ክፍል የተውጣጡ ከፍተኛ ባለሰልጣናት፣ የሃይማኖት አባቶችና ባለሀብቶችን  ጨምሮ ሌሎች 465 ሰዎችን ይዞ ይጓዛል ተብሏል።

ወደ አስመራ የሚሄደውን የልዑካን ቡድን  የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ  ይመሩታል ተብሏል።

ይህን ቡድን የሚመሩት አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ እንደተናገሩትም “ጉዞው ኢትዮጵያ ለጀመረችው የለውጥ እንቅስቃሴ አንዱ አካል ነው” ብለዋል።

የለውጥ አንቅስቃሴው የሁለቱ አገራት ግንኙነትን የጥላቻ ግድግዳ ሰብሮ “ታይቶ የማይታወቅ አዲስ የፍቅር ግንኙነት ይጀምራልም ብለዋል።

አየር መንገዱ በአፍሪካ ቀዳሚ መሆኑ ለሁለቱ አገራት ህዝቦች ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካ ኩራት በመሆኑ ልንከባከው ይገባል ነው ያሉት።

በአፍሪካ ህብረት የኤርትራ ተወካይ አምባሳደር አርዓያ ደስታ በበኩላቸው አየር መንገዱ ወደ አስመራ በረራ መጀመሩ “የሁለቱን አገራት ህዝቦች የበለጠ ለማቀራረብ እድል ይሰጣል”።

አየር መንገዱ ወደ አስመራ በረራ መጀመሩ ከፍተኛ ደስታ እንደፈጠረባቸውም አምባሳደር አርዓያ ደስታ ገልጸዋል።

ዛሬ በሚደረገው በረራ ዶክተር አርከበ እቁባይ፤ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ፤ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማያም ደሳለኝና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ማቲያሰን ጨምሮ ሌሎች 465 ሰዎች ይጓዛሉ። (ኢዜአ)