የሥራ ማቆም አድማ ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ ቀላል ባቡር ሠራተኞች በዛሬው ዕለት ሥራ መጀመራቸውን አስታወቁ ።
የቀላል ባቡር ሠራተኞቹ ከ3ዓመት በላይ የቆየ መብቶቻቸውንና ጥቅማጥቅሞቻቸው ለማስከበር ለኮርፖሬሽኑና ለሚመለከታቸው አካላት ጥያቄ አቅርበው ምላሽ በማጣታቸው ምክንያት በትናንትናው ዕለት የሥራ ማቆም አድማ ማድረጋቸውን መግለጻቸው ይታወሳል ።
ሠራተኞቹ ያልተመለሱላቸውን ጥያቄዎች ለኮርፖሬሽኑ ማቅረብ እንደሚቀጥሉ በመግለጽ የቀላል ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ተጠቃሚ የሆነው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ እንግልት እንዳይደርስበት ሥራቸውን በዛሬው ዕለት መጀመራቸውን ገልጸዋል ።
የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ብርሃኑ በሻህ በበኩላቸው ሠራተኞቹ ያነሱት ጥያቄ አግባብነት የጎደለው መሆኑን ተናግረዋል ።
ሠራተኞቹ ጥያቄያቸውን ማቅረብ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ 90 በመቶ የሚሆነው ጥያቄያቸው ምላሽ መሠጠቱንና ሠራተኞቹ የሚያነሱት ጥያቄዎች ሌላ ዓላማን ያነገበ በመሆኑ ኮርፖሬሽኑ እርምጃ ለመውሰድ እንደሚገድድ ገልጸዋል ።
ሠራተኞቹ በበኩላቸው በተለያዩ ጊዚያት ያነሷቸው ጥያቄዎች በአግባቡ አለመመለሳቸውን በማስረጃ ጭምር ማቅረብ እንደሚችሉና ጥያቄያቸው ከሌላ ዓላማ ጋር ሊያያዝ እንደማይችል ለዋልታ ተናግረዋል ።
የኮርፖሬሽኑ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደረጄ ተፈራ ኮርፖሬሽኑ ከሠራተኞቹ ጋር ስምምነት ላይ በመድረሱ በዛሬው ዕለት ቀላል ባቡሩ አገልገሎት መሥጠት መጀመሩን አስረድተዋል ።