የኮንታ ልዩ ወረዳ ነዋሪዎች ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የድጋፍ ሰልፍ አደረጉ

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት በኮንታ ልዩ ወረዳ የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ለኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የድጋፍ ሰልፍ አድርገዋል፡፡

በድጋፍ ሰልፉ ላይ የተሳተፉ የህብረተሰብ ክፍሎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሀገሪቱ ላይ እያስመዘገቡ ያሉትን ለውጥ ከጎናቸው በመሆን እንደሚደግፉና የለውጡ አካል እንደሚሆኑ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በአካባቢያቸው ከፍተኛ የሆነ አስተዳደራዊ በደል ይደርስበት እንደነበረ ያስታወሱት አስተያየት ሰጪዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ከመጡ 100 ቀናት ውስጥ በመጠኑም ቢሆን መሻሻል ማሳየቱን ገልጸዋል፡፡   

ይሁን እንጂ በክልሉም ሆነ በልዩ ወረዳው ከፍተኛ የሆነ የመልካም አስተዳደር እጦት በመኖሩ ህዝቡ ለከፍተኛ ችግር እና እንግልት መዳረጉን ተናግረው ይህም በአፋጣኝ እንዲሻሻል በሰልፉ ላይ ጠይቀዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በመልካም አስተዳደር እጦት ምክንያት የጠፋ የህዝብና የሀገር ንብረት እንዲመለስ እና ጥፋተኛ የሆኑ አመራሮች ከስልጣን ወርደው እንድጠየቁ በአፅንኦት ያሳሰቡ ሲሆን መንግስት ትኩረት ሊያደርጉባቸው ይገባል ያሉትን ዋና ዋና ነጥቦች በአቋም መግለፃቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡

የድጋፍ ሰልፉ ተሳታፊ የልዩ ወረዳ ነዋሪዎቹ ለሠላም እና ለሀገር ልማት በሰላማዊ መንገድ ትግላቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አስታውቀዋል፡፡

በሌላ በኩል በጋሞ ጎፋ ዞን ሳውላ ከተማም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የድጋፍ ሰልፍ ተካሂዷል፡፡