ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችን አወያዩ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ  የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችን አወያይተዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ 22 ከሀገር አቀፍና 30 ከተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች የተውጣጡ  የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች መገኝታቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር /ቤት መረጃ ያስረዳል።

የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎቹ በውይይቱ ላይ እንደተናገሩት በሀገር ቤትና በቀጠናው አካባቢ በተለያዩ እስር ቤቶች የሚገኙ እስረኞችን ከእስር ቤት እንዲወጡ መንግስት ያከናወናቸው ተግባራት የሚደነቁ ናቸው።

የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች በሀገሪቱ የምርጫ ህግና አፈፃፀሞች ላይ ለውጦች መደረግ እንዳለባቸው ማመላከታቸውም ነው የተገለጸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በበኩላቸው የመድበለ ፓርቲ ሥርዓትን ከማረጋገጥ ውጭ ለሀገሪቱ የተሻለ አማራጭ የሌላት መሆኑን ገልፀዋል።

መድበለ ፓርቲ ስርዓት በሃገሪቱ የተለያዩ አመለካከቶችን በሰላማዊ መንገድ በማስተናገድና በመፍታት ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሚያስችል መሆኑንም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለፁት።

የሰብዓዊ መብትንና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ዴሞከራሲያዊ አሰራሩ በጠንካራ ተቋማት መታገዝ እንዳለበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ጋር በተወያዩበት መድረክ ላይ አንስተዋል።