ተገቢ ባልሆነ መንገድ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተባረው የነበሩት መምህራን ወደ ስራቸው ይመለሳሉ – ዶክተር አቢይ አህመድ

ከዚህ ቀደም ተገቢ ባልሆነ መንገድ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተባረው የነበሩት መምህራን ወደ ስራቸው እንደሚመለሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን የተናገሩት ከዩኒቨርስቲ መምህራን ጋር በሚወያዩበት ወቅት የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ጥላዬ ጌቴ ያቀረቡትን ጥያቄ ተከትሎ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ 3 ሺህ 175 ከሚሆኑ እና ከ 50 ዩኒቨርሲቲዎች ከተወጣጡ መምህራን ጋር በጠቅላይ ሚኒስቴር የመሰብሰቢያ አዳራሽ  ውይይት አካሂደዋል፡፡

በውይይቱ ወቅትም ከተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎች ቀርበዋል፡፡

ጥያቄዎቹ በትምህርት ጥራት፣ ፖሊሲ፣ ብቃት እና ስነ ምግባር ያለው ዜጋ ስለማፍራት እንዲሁም ጥናት እና ምርምር ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡

በተጨማሪም የሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ፣ ብልሹ አሰራር እና ሙስና እና ሀገራዊ አንድነት እና በመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ ጥያቄዎች ቀርበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩም ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽ በመስጠት ከተሳታፊዎቹ ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር በትምህርት ተቋማት ውስጥ ያሉ ብልሹ አሰራሮች እና በፖለቲካ አመለካከት እና በሌሎች ሰበቦች የሚደረጉ አድልኦዎች እንደሚስተካከሉም ቃል ገብተዋል፡፡

መንግስት የትምህርትን ጥራት ለማረጋገጥ በከፍተኛ ተነሳሽነት እየሰራ እንደሆነ እና ወደፊትም ይሄው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

መረጃውን ያደረሰን የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት ሚድያ ዶክመንቴሽን እና ፕሬስ ሴክሬታርያት ነው፡፡