ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የአሜሪካ የመደመር ጉዞ ዝግጅት እየተካሄደ ነው

የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ‘የመደመር ጉዞ ወደ አሜሪካ’ የተሳካ እንዲሆን ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለፀ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፊታችን ቅዳሜ ሐምሌ 21 ቀን 2010 ዓም ጀምሮ ለሶሰት ቀናት በአሜሪካ በሚያደርጉት ጉብኝት በዋሽንግተን ዲሲ፣ ሎስ አንጀለስ እና ሚኒሶታ በመገኘት ለመጀመሪያ ጊዜ በሰሜን አሜሪካ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ጋር ይወያያሉ፡፡

ጉብኝቱን ለማስተባበር በሶስቱ ከተሞች የተቋቋሙት አካላትም ዝግጅታቸውን አጠናክረው መቀጠላቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት በላከው መግለጫ ጠቅሷል።

የውይይት መርሃ-ግብሩ የተዘጋጀው ሰሜን አሜሪካ ቢሆንም በመላው ዓለም የሚኖሩ የዳያስፖራ አባላት የዝግጅቱ አካል ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የውይይት መርሃ-ግብሩን በአገር ውስጥና በውጭ መገናኛ ብዙሃን በቀጥታ ለህዝብ ተደራሽ  ለማድረግም ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነም መግለጫው አመልክቷል።(ምንጭ: የውጭ ጉዳይ  ቃል አቀባይ  ጽህፈት ቤት)