የፕሬዚዳንቱና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የህይወት ተሞክሮ አቅም ይፈጥርልናል — የሜዳሊያ ተመራቂዎች

ከኢፌዴሪ ፕሬዚዳንትና ጠቅላይ ሚኒስትር ያገኙት የህይወት ተሞክሮ  ለወደፊት ዓላማቸው ስኬት  አቅም እንደሚፈጥርላቸው በሜዳሊያ የተመረቁ ተማሪዎች ገለፁ።

ዘንድሮ ከመንግስትና የግል ዩኒቨርሲቲዎች ከተመረቁት ተማሪዎች መካከል ከፍተኛ ውጤት በማምጣት የሜዳሊያ ተሸላሚ የሆኑ ከ400 በላይ ምሩቃን በተያዘላቸው መርሃ-ግብር መሠረት ከከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ጋር በመወያየት ላይ ናቸው።

በዚህም  ከፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ እና ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር በተዘጋጁ መድረኮች ላይ ተወያይተዋል።

ምሩቃኑ  በሰጡት አስተያየት በተለይ ከፕሬዚዳንቱ እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ያደረጉት ቆይታ ያገኙት የህይወት ተሞክሮና የዓላማ ጽናት ትምህርት ሰጥቷቸዋል ።

ወጣት ነዋል መሐመድ ከአድማስ ዩኒቨርሲቲ የማኔጅመንት የሚዳሊያ ምሩቅ “ትልቅ ተስፋና ወደፊት ደግሞ ብሩህ ተስፋ ይዘን ወደ ትልቅ ደረጃ ማድረስ እንደምንችል ከዶክተር አብይ አህመድም ከፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ትልቅ ንግግር ተደርጎልናል፤ እኛም ትልቅ ነገር ሰርተን ይህችን አገር ወደ ላቀ ደረጃ እናደርሳለን ብለን እናምናለን።

ወጣት ትዕግስት ግሩም ከመቱ ዩኒቨርሲቲ በደን ሳይንስ የሜዳሊያ ምሩቅ በአስተያየቷ”ህይወታችንን የምንመራበት መንገድና አቅጣጫ አሳይተውናል” ብላለች፡፡

በዩኒቨርስቲ ቆይታ የቀሰሙትን ዕውቀት ወደ ተግባር በመለወጥ ማህበረሰቡን በማንኛውም መንገድ ለማገልገል፤ የሚጠበቅባቸውን ሀገራዊ ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት የበለጠ መነሳሳት የፈጠረላቸው መሆኑንም ምሩቃኑ ገልፀዋል።

“ኢትዮጵያ አገራችንን አሁን ካለችበት ከፍ ያለ ደረጃ ላይ እንድትደርስ በተማርኩበትና ባለኝ ሙያ መሰረት ህዝቤንና አገሬን እንዳገለግልና እኔ ባገለገልኩት በሰጠሁት ምላሽ ደስተኛ እንዲሆንና ህዝቤን ለማገልገል በመወሰን በሙሉ ተስፋ ተነስቻለሁ።” በማለት የተናገረው ወጣት ተክላይ ኪዳነ ገብረማርያም በአዲግራት ዩኒቨርሲቲ የሲቪል ምህንድስና የሜዳሊያ ምሩቅ ነው፡፡

ምሩቃኑ ለኢትዮጵያ እድገት መስራት፣ ያስተማራቸውን ህብረተሰብ በቅንነት ማገልገልና የመሪነት ሚናቸውን መወጣት ቀጣይ የቤት ስራቸው እንደሆነም ገለጸዋል።

ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በበኩላቸው ወጣቶች የነገ ኢትዮጵያ ተረካቢዎች መሆናቸውን በመገንዘብ ለኢትዮጵያ እድገትና ስልጣኔ ከዛሬ ጀምሮ ተግተው መስራት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።(ኢዜአ)