ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሞት ማዘናቸውን ገለጹ

ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሞት ማዘናቸውን ገለጹ።

ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ትናንት ማለዳ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ መኪናቸው ውስጥ ሞተው መገኘታቸው የሚታወስ ነው።

ፕሬዚዳንቱ በዚሁ የሀዘን መግለጫቸው ኢንጂኒር ስመኘው የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ ወደ አንድ ምዕራፍ ያሸጋግራል ተብሎ የሚጠበቀውን እና ኢትዮጵያዊያን ታላቅ ተስፋ ያሳደሩበትን የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ዳር ለማድረስ ሲደክሙ የነበሩ ውድ የሀገር ልጅ መሆናቸውን ገልፀዋል።

“የግድቡን  ግንባታ እውን ለማድረግ ከህዝቡ የተቀበለውን አደራ ለመወጣት ሰለቸኝ ደከመኝ ሳይል ሲታትር የነበረው ውድ የኢትዮጵያ ልጅ ኢንጂነር ስመኘው በቀለን ድንገተኛ የህልፈት ዜና የሰማሁት በከፍተኛ የልብ ስብራት ነው” ሲሉ ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።

ኢንጅነር ስመኘው ለዘመናት የህዝብ ቁጭት የነበረውን የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ወደሚፈለገው ደረጃ ለማድረስ በከፍተኛ የሀገር ፍቅር ስሜት የሰሩ እና ለሌሎች አርኣያ የሚሆኑ ታላቅ የልማት አርበኛ መሆናቸውንም ፕሬዘዳንቱ ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያውያን የዘመናት ቁጭት የሆነውን አባይን በጋራ እና ፍትሃዊ በሆነ መልኩ የማልማት ፍላጎት ውጤት የሆነውን ግድብ እውን ለማድረግ የፈጸሙት ተግባር መልካም ኢትዮጵያዊ አሻራው እንደማይጠፋ ተናግረዋል።

“ኢንጅነር ስመኘው በቀለ እንደ ልጁ የሚቆጥረው እና ብዙ የደከመበት የህዳሴ ግድብ ተጠናቆ ለማየት አለመብቃቱ ሃዘናችንን መራር ቢያደርገውም የግድቡ ግንባታ በኢትዮጵያውያን እና በመንግስታችን የተቀናጀ ርብርብ አልቆ የኢንጅነር ስመኘውና የሌሎች ሰማዕታትን ምኞት ህያው እንደምናደርገው ሙሉ እምነቴ ነው” ሲሉም ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ገልፀዋል።

ለኢንጅነር ስመኘው በቀለ ቤተሰቦች፣ የስራ ባልደረቦችና መላው የኢትዮጵያ ህዝብ መጽናናትን ተመኝተዋል።

በተመሳሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም በኢንጅነር ስመኘው በቀለ ድንገተኛ ህልፈተ ህይወት የተሰማውን ሀዘን ገልጿል።

ሚኒስቴሩ ባወጣው የሀዘን መገለጫ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ መሰረተ ድንጋይ ከተጣለበት እለት አንስቶ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ግድቡን ለፍፃሜ ለማድረስ የተጣለባቸውን ታላቅ አገራዊ ሃላፊነትና አደራ በብቃት እና በሃገር ፍቅርና ስሜት መወጣታቸውን አመልክቷል።

ለቤተሰቦቻቸው፣ ለስራ ባልደረቦቻቸውና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መጽናናትን ተመኝቷል።(ኢዜአ)