የፍትህ ተቋማት የምህረት አዋጁን በጥንቃቄ እንዲያስፈጽሙ ጠቅላይ አቃቢ ህግ አሳሰበ

የፍትህ ተቋማት የምህረት አዋጅን በጥንቃቄ እንዲያስፈጽሙ የፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ አሳሰበ።

 

በተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች ውስጥ ለተሳተፉ ሰዎች መንግስት ምህረት ለመስጠት ሃምሌ 13 ቀን 2010 ዓ.ም አዋጅ 1096/2010ን ማጽደቁ ይታወሳል።

 

በዚህም የፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ የምህረት አዋጁን አፈጻጸም በተመለከተ ከፌደራልና ከክልል የፍትህ ተቋማት፤ከሃይማኖት አባቶችና አገር ሽማግሌዎች ጋር በአዲስ አበባ ውይይት አካሂዷል።

 

በአገሪቱ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታን ለማሳደግና የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት፤የጥላቻና የእርስ በርስ ጥርጣሬን በማስወገድ ብሄራዊ መግባባትን ለመፍጠር በማሰብ አዋጅ 1096/2010 አዋጅ ጸድቆ ተግባራዊ እየተደረገ  ይገኛል።

 

የፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ ፕሬዝዳንት አቶ ብርሃኑ ጸጋየ በውይይቱ ላይ እንዳሉት በአገሪቱ ተከስቶ የነበረውን ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ተከትሎ በተወሰኑ የወንጀል ድርጊት ውስጥ ለተሳተፉ ሰዎች መንግስት የወንጀል ተጠያቂነታቸውን ሰርዟል።

 

በዚህ ሁሉም የፍትህ ተቋማት በአዋጁ አፈጻጸምና አተገባበር ዙሪያ ወጥ የሆነ አሰራርን እንዲከተሉና ግለጽ መረጃ እንዲኖራቸው ለማድረግ ውይይት መደረጉንም ጠቁመዋል።

 

የምህረት አዋጁ ከግንቦት 30/2010 ዓ.ም በፊት የተፈጸሙ ምህረት የሚያሰጡ የወንጀል ድርጊቶችን ሁሉም ተቋማት ተገንዝበው ወጥ በሆነ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ እንዲከውኑ አቶ ብርሃኑ አሳስበዋል።

 

የህገ መንገስታዊ ስልጣንን ተግባራዊነት በማሰናከል፤የጦር መሳሪያ ይዞ በማመጽ፤የእርስ በርስ ጦርነት በማስነሳት ፤የሃገሪቱን የፖለቲካና የግዛት አንድነት በመንካት ወንጀል የተጠረጠሩ፣የተፈረደባቸውና በክስ ሂደት ላይ ያሉ ሰዎች በምህረቱ አዋጁ መሰረት ይለቀቃሉ።

 

በተጨማሪም የሃገር መከላከያ ሃይልን በመጉዳት፤በሃገር መክዳት፤ከጠላት ጋር መተባበር ፤በስለላ ወንጀል የተሰማራ የተንኮል ድርጊቶችን ያሰናዳ፤በኩብለላና የሃሰት ወሬዎችን በማውራት ህዝብን ለአፍራሽ ስራ በማነሳሳት ወንጀሎች የተከሰሱና የተፈረደባቸው ሰዎችም በምህረት አዋጁ ይካተታሉ።

 

እንደ ፕሬዝዳንቱ ገለጻ በጸረ ሽብር አዋጅ ቁጥር 652/2001 ስር የተመለከቱትን የወንጀል ድንጋጌዎች በመተላለፍ የተፈጸመ ወንጀል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ 01/2009 እና 2/2010 ላይ የተመለከቱትን የወንጀል ድንጋጌዎች ተላለፈው ወንጀል የፈጸሙትም በዚህ አዋጅ ምህረት አግኝተዋል።

 

ይሁንና ምህረት የተደረገለት ማንኛውም ሰው ንብረቱ እንዲወረስ በፍርድ ቤት የተወሰነበት ሰው ወይም ተቋም የተወረሰውን ንብረት እንዲመለስለት የመጠየቅ መብት እንደሌለው የምህረት አዋጁ ደንግጓል።

 

ይሁን እንጅ ከላይ በተገለጹት ወንጀሎች በሙሉ ምህረት የተደረገ ቢሆንም በሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር  652/2001 አንቀጽ 3 ንዑስ አንቀጽ 1 የተመለከተውን በመተላለፍ የሰው ህይወት ያጠፋና ጉዳዩ በፍርድ ሂደት ላይ ከሆነ በዚህ አዋጅ ላይ ምህረት አይደረግለትም ብለዋል።

 

ከላይ ከተዘረዘሩት የወንጀል አይነቶች ውጪ በሌሎች ወንጀሎች ተሳትፈው በማረሚያ ቤት የሚገኙ ሰዎች የምህረት አዋጁ እንደማይመለከታቸው  አቶ ብርሃኑ ገልጸዋል።

 

በተሳሳተ አመለካከት በሌላ ወንጀል ማረሚያ ቤት የሚገኙ ታራሚዎች ከእስር መፈታት አለብን በማለት ሁከትና ብጥብጥ ለማስነሳት ሲሞክሩ ይስተዋላል ያሉት ፕሬዝዳንቱ መንግስት ምህረት ካደረገባቸው ወንጀሎች ውጭ ያሉ ታራሚዎችን ፍርዳቸውን መጨረስ አለባቸው ብለዋል።

 

ማንኛውም ሰው በምህረቱ ተጠቃሚ መሆን አለመሆኑን በጥንቃቄ መገንዘብ እንደሚኖርበትና የፍትህ ተቋማትም አዋጁን በሚያስፈጽሙበት ጊዜ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ፕሬዘዳንቱ አሳስበዋል።

 

የምህረት አዋጁ ተጠቃሚ የሆኑት አዋጁ ከታወጀበት ሃምሌ 13 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት ስድስት ወራት ውስጥ በፌደራል ወይም በክልል ፍትህ ቢሮዎች ከታች በተቀመጡ መንገዶች አማካኝነት ሪፖርት ማድረግ እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።

 

የምህረቱ ተጠቃሚዎች ለዚሁ ብቻ በተዘጋጀው የተቋሙ ድህረ ገጽ www.fag.gov.et በመጠቀም በተዘጋጀው የመመዝገቢያ ፎርም መሰረት መመዝገብ እንደሚችሉና በስልክ ቁጥር 0115515099 በመደወል ማመልከት ይችላሉ ተብሏል።

 

ነገር ግን በምህረት አዋጁ መሰረት የተለቀቁ ሰዎች በተቀመጠው የማሳወቂያ መንገድ ሪፖርት ሳያደርጉ ቢቀሩ ምህረቱን እንዳልተቀበሉ ተቆጥሮ የምህረት ተጠቃሚነት መብታቸውን እንደሚያሳጣቸው ፕሬዘዳንቱ አስታውቀዋል።