ምርጫውን ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ የፖለቲካ ምህዳሩን የማስፋት ሥራ እየተከናወነ ነው- ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ

 ከሁለት ዓመት በኋላ የሚካሄደው ሀገር አቀፍ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የፖለቲካ ምህዳሩን የማስፋት ስራ እየተከናወነ መሆኑን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለፁ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአሜሪካ ጉብኝታቸው ከትናንት በስተያ ማምሻውን ከሲቪክ ማህበረሰብ ተወካዮች እና ከኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ምሁራን ጋር ሰፊ ውይይት አድርገዋል።

በውይይቱ ላይ ተሳታፊዎቹ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተለያዩ ጥያቄዎችን አንስተው ምላሽ ተሰጥቷቸዋል።

በምላሻቸውም ላይ ከሁለት ዓመት በኋላ የሚካሄደው ሀገር አቀፍ ምርጫ ፍፁም ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን መንግስት ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ነው ያነሱት።

በተለይም የፖለቲካ ምህዳሩን የማስፋቱ ስራ በመከናወን ላይ ይገኛል ብለዋል።

የፕሬስ እና የምርጫ ህጎችን የማሻሻሉ ስራ ከእነዚህ ተግባራት መካከል አንዱ መሆኑንም ነው የጠቀሱት።

ከፀረ ሽብር ህጉ ጋር ተያይዘው ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፥ በየትኛውም ሀገር የፀረ ሽብር ህግ እንዳለ ጠቁመዋል። የሚያስፈልገው ይህ የፀረ ሽብር ህግ ለፖለቲካ ጥቅም እንዳይወል ማድረግ ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ፓርቲያቸው ኢህአዴግ ከሁለት ዓመት በኋላ ለሚካሄደው ምርጫ ከወዲሁ እየተዘጋጀ መሆኑን የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የዚህን ምርጫ ውጤት ተቀብሎ ካሸነፈ ለመቀጠል ከተሸነፈም ስልጣን ለማስረከብ ዝግጁ እንደሆነ አረጋግጠዋል።

ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ልዩነታቸውን አጥብበው ከመከፋፈል ባህላቸው ወጥተው አንድ በመሆን ወደ ተፎካካሪነት መሸጋገር እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በተለያየ ምክንያት ከሀገር የተሰደዱ ግለሰቦችም የምህረት አዋጁን በመጠቀም ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል።(ኤፍቢሲ)