የዋሽንግተን ዲሲ ከተማ ሐምሌ 21 ቀንን ”የኢትዮጵያውያን ቀን” አድርጎ ሰየመ

የዋሽንግተን ዲሲ ከተማ ሐምሌ 21 ቀንን ”የኢትዮጵያውያን ቀንአድርጎ ሰየመ።

የዋሽንግተን ዲሲ ከንቲባ ሙሪየል ቦውሰር ሐምሌ 21 ቀን የኢትዮጵያዊያን ቀን ሆኖ አንዲታሰብ ያወጁት በአሜሪካ ጉብኝት እያደረጉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድን ጨምሮ ከ25 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን በታደሙበት ዝግጅት ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።

ከንቲባዋ በዚሁ ጊዜ ባደረጉት ንግግር ጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር ዓብይ ስልጣን ከያዙበት ጊዜ አንስቶ በሀገሪቱ ያለውን የሰብአዊ መብት ሁኔታ ለማሻሻልና ከኤርትራ ጋር የነበረውን ችግር ለመፍታት እንደዚሁም ምጣኔ ኃብታዊና ፖለቲካዊ ለውጦችን ለማምጣት የወሰዷቸው እርምጃዎች በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ማህበረሰብን ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት እንደሚያጠናክረው ገልፀዋል።

አክለውም ለዛሬዋ ዋሽንግተን እውን መሆን በከተማዋ የሚኖሩት ኢትዮጵያዊያን ማህበረሰብ አባላት ሚና የላቀ መሆኑን የጠቀሱት ከንቲባዋ  በዋሽንግተን እና በአዲስ አበባ ከተሞች መካከል ያለውን እህትማማች ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር ዓብይ በበኩላቸው ”ስንደመር የምናምር ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ቀን ማወጅ እንችላለን” ሲሉ ተደምጠዋል።

”ግንቡን እናፈርሳለን ድልድዩን እንገነባለን” በሚል መሪ ሀሳብ አሜሪካ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዋሽንግተን ኮንቬንሽን አዳራሽ 25 ሺህ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በተገኙበት ንግግር አድርገዋል።

በንግግራቸውም “ኢትዮጵያዊነት በአካል አገር ወስጥ ስንኖር ብቻ የሚኖር ስንወጣ የሚሸሽ ጥላ አለመሆኑን፣ኢትዮጵያዊነት ከደማችን የተዋሃደ ከአጥንታችን ጋር የፀና በልባችን የታተመ መሆኑን ለማየት ችያለው” ብለዋል።

ኢትዮጵያ ማህፀነ-ለምለም ብትሆንም ከልጆቿ የሚገባትን ያህል እየተጠቀመች አለመሆኑን የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህም ምክንያቱ ጥላቻ፣ ቂም፣ በቀል፣ የጅምላ ጥላቻ የተባሉ ሾተላዮች ናቸው” በማለት ጠቅሰዋል።

በመሆኑም በመጪው ጊዜ የጥላቻንና የመራራቅን ግንብን በማፍረስ የኢትዮጵያን ታላቅነት ማብሰር ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

ግንብ ማፍረስ ብቻ በቂ ባለመሆኑ ድልድዩን ለመገንባት ሁሉም ተዋናይ እንዲሆን ጠይቀዋል። የምንገነባው ድልድይ ለኛ ብቻ ሳይሆን ለትውልድ የሚተርፍ መሆን አለበትም ብለዋል።

”ኢትዮጵያ የሁላችንም እናት ነች፤ ከተባበርን ዛሬም የአድዋን መሰል ታሪክ እንሰራለን” ሲሉ ተናግረዋል።

“እንደመር ያልነው ለልህቀት፣ታላቅ ሀገር ለመገንባት መሆኑን ጠቅሰው ውጭ የምትገኙ ኢትዮጵያውያን የኢኮኖሚ አጋዣችን ብቻ ሳይሆኑ የሰላም ማማ ናቸው” ብለዋል፡፡

መጪው ጊዜ ታላቅ ኢትዮጵያን በመፍጠር በልጆቿ ፊት ደስታና ሳቅ የምናይበት የለውጥ ጉዞ መሆን እንዳለበትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ  አሳስበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚንስትሩ በጉብኝታቸው የአሜሪካው ምክትል ፕሬዚዳንት ማይክል ፔንስን ጨምሮ በአሜሪካ ከሚኖሩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ከእስልምናና ክርስትና የሀይማኖት መሪዎች፣ ከአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት እና ሌሎች ተቋማት ጋር ተወያይተዋል።(ኢዜአ)