የጌዴኦና የጉጂ ህዝቦች ለዘመናት የገነቡት አብሮነት ላይነጣጠል የተሳሰረ ነው – የጌዴኦና ጉጂ አባ ገዳዎች

የጌዴኦና የጉጂ ህዝቦች ለዘመናት የገነቡት አብሮነት ላይነጣጠል የተሳሰረ መሆኑን የጌዴኦና ጉጂ አባ ገዳዎች ተናግረዋል፡፡

አባገዳዎቹ ይህንን የተናገሩት በምዕራብና ምስራቅ ጉጂ ዞኖችና በጌዴኦ ዞን አጎራባች አከባቢዎች የተከሰተውን ግጭት በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል የሰላም ኮንፍራንስ በተካሄደበት ወቅት ነው፡፡

የኮንፍረንሱ ተሳታፊዎች የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደ ቄያቸው በመመለስና በግጭቱ ውስጥ ተሳታፊ የነበሩ ግለሰቦችን በህግ ቁጥጥር ስር በማዋል የዜጎችን ደህንነት በዘላቂነት የማስጠበቁን ስራ መንግስት በትኩረት እንዲሰራ ጠይቀዋል፡፡

ማንም ሰው በማንነቱ መገፋት የለበትም ያሉት የጉጂ አባጋዳ ጂሎ ማኖ በሁሉቱ ህዝቦች መካከል ችግር ሊፈጥሩ የሚንቀሳቀሱ ሀይሎች ከአሁን በኋላ          ምንም አይነት ቦታ ሰለማይኖራቸው ወጣቶች ይህን በመረዳት እራሳቸውን ከእኩይ ተግባር እንዲሰበስቡ አሳስበዋል፡፡

የጌዴኦ አባገዳ ዳንቦብ ማሮ በበኩላቸው የጌዴኦና የጉጂ ህዝቦች ወንድማማች ህዝቦች ከመሆናቸውም ባለፈ ለዘመናት የገነቡት አብሮነት ላይነጣጠል የተሳሰረ ነው ብለዋል

የጎንዶሮ ስርዓት የፈረሰበትን ምክንያት በስፋት ውይይት በማድረግ አሁን ሠላም ማውረድ ስለቻልን የእኛ የሆናችሁ ህዝቦች በሙሉ እርቀ ሠላም እንድታወርዱና እንዳለፈው ጊዜ በጋራ በፍቅር እንድትኖሩ ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደ ቄያቸው በመመለስና በግጭቱ ውስጥ ተሳታፊ የነበሩ ግለሰቦችን በህግ ቁጥጥር ስር በማዋል የዜጎችን ደህንነት በዘላቂነት የማስጠበቁን ስራ መንግስት በትኩረት እንዲሰራም ጠይቀዋል

የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሃይለማሪያም ተስፋዬ በበኩላቸው ግጭት ለጌዴኦም ሆነ ለጉጂ ህዝብ የሚያስገኘው ጥቅም ባለመኖሩ ለዘላቂ ሠላም ሁሉም ሰው በትኩረት እንዲሰራ ጥሪ አቅርበዋል

የምዕራብ ጉጂ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበራ ቡኖ በበኩላቸው ህብረተሰቡ በተለይም ወጣቶች የጥፋት ሃይሎችን አጋልጦ ለህግ በማቅረብ ተፈናቃዮችን ለማቋቋም የሚደረገውን ጥረት እንዲደግፉ ጠይቀዋል

ወጣቶች በበኩላቸው በቀጣይ ተፈናቃዮች ወደ አከባቢያቸው ሲመለሱ ተገቢውን ድጋፍ በማድረግ ህዝብን ለመካስ ዝግጁ ነን በማለት ተናግረዋል፡፡

የፌዴራል አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኢታ አቶ ካይዳኪ ገዛሄኝ በበኩላቸው የጌዴኦና ጉጂ ህዝቦች በባህል በቋንቋና በደም የተሳሰሩ አንድ ህዝብ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ግጭት አፈታቱ ባህላዊ ስርዓትን በመጠቀም ከዘመናዊ ጋር በማዋሃድ ለማከናወን በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ሠላም መውረዱ ለመንግስትም ሆነ ለህዝቡ ትልቅ ድል ሲሆን በቀጣይም የህግ የበላይነት ለማረጋገጥ ለሚሰሩ ሥራዎች መደላድልን እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ መርማሪ ቡድን ወደ ሥራ በመግባቱ በሁለቱም በኩል ማህበረሰቡ ወንጀለኞችን አሳልፎ በመስጠት በአንድ በኩል ለተፈናቀሉ ዜጎች አስተማማኝ ሰላም መኖሩን ለማረጋገጥ በሌላ በኩል እርቀ ሠላሙ ዘላቂ እንዲሆን የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት እየተወጡ ይገኛሉ ፡፡/ የጌዴኦ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን/