ጠ/ሚ ዶክተር ዐብይ በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሃገራቸው ጉዳይ ቀጥተኛ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪ አቀረቡ

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሃገራቸው ጉዳይ ቀጥተኛ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪ አቀረቡ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአሜሪካ ሎስ አንጀለስ ከኢትዮጵያውያን ጋር ትናንት ተወያይተዋል።

በውይይቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያውያን ባለፉት ጊዜያት ብዙ ዋጋ መክፈላቸውን ጠቅሰው፥ ኢትዮጵያን ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማድረስ ሁሉን አቀፍ ርብርብ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም በድህነት የሚኖሩ ወገናቸውን በተለይም፥ በመሠረተ ልማት፣ የትምህርትና ሌሎች ማህበራዊ ተቋማትን በማስፋፋት ረገድ ሊያግዙ እንደሚገባም ነው የተናገሩት።

አንድነትና መተባባር ድህነትን ለመቅረፍ ከሚደረገው ጥረት ባሻገርም፥ ብልሹ አሰራርና ሙስናን ለመዋጋት አጋዥ በመሆኑ በዚህ ረገድም መተባበር ይገባል ነው ያሉት።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው የአንድ መሪ የሥልጣን ጊዜ ከሁለት ጊዜ በላይ እንደማይሆንም አንስተዋል።

ሃገሪቱን በሁሉ መስክ ለመገንባት በሚደረገው ጥረትም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ድርሻ የጎላ መሆኑን ጠቅሰው፥ ከዚህ አንጻርም ኢትዮጵያውያኑ ሃገራቸው በመግባት በእውቀታቸውና በገንዘባቸው የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

ኤምባሲዎች እና አምባሳደሮች ኢትዮጵያውያን ያሉበት ቦታ እያነፈነፉ እውቀታቸውን ወደ ሀገራቸው እንዲያመጡ ማድረግ ይገባቸዋልም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው።

ይህ እንዲሳካም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጠንካራ የማሻሻያ ስራ መጀመሩንም አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያውያን በእረፍት ጊዜያቸው ወደ ሀገራቸው በመምጣት ሃገራቸውን ሊያግዙ እንደሚገባም ጠይቀዋል።

ከኢትዮ ኤርትራ ግንኙነት ጋር በተያያዘም በእንዲህ ዓይነቱ ስብስብ ውስጥ ኤርትራውያን ወንድሞች እና እህቶችን በማካተት ግንኙነትን ማስተካከል እንደሚገባ መክረዋል።

ወጣቱ መቼ ከኢትዮጵያ እንደሚወጣ በማሰብ ግብረ ገብነት ፈርሷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ መንግስት የወጣቱን ስነ ልቦና መገንባትና ህግ የሚያከበርና ሀገሩን የሚወድ ወጣት መፍጠር ነው ዓላማ እንዳለው አስረድተዋል።

እርሻን በተመለከተ በተለይ በረሃማ አካባቢዎች እምብዛም እንዳልተሰራባቸው በመጥቀስ፥ ከ2011 በጀት ከፍ ያለው ገንዘብ የተመደበው ለግብርና በመሆኑ በ2011 በጀት ዓመት ለመስኖ እርሻ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ጠቅሰዋል።

ከደህንነታቸው ጋር ተያይዞ ለተነሳላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ደግሞ፥ ለሀገር እየሰራሁና ለሀገር እየተጋሁ ምንም ዓይነት ሞት ቢመጣ ክብር አድርጌ እወስደዋለሁ በማለት መልሰዋል።

ሰዎች እንዳትሮጥና ቀንና ማታ እንዳትሰራ ሞት እና ፍርሃትን ቢያውጁም ሞትና ፍርሃት ከጉዞ እንደማያቆም ማሳየት ይገባል ብለዋል በምላሻቸው።

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር መለያየትን በማስወገድ ለሃገሪቱ ሁለንተናዊ ለውጥ መተባበር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም በእውቀትና ሃብታቸው በሃገራቸው ግንባታ ላይ እንዲሳተፉም ጠይቀዋል።

የሎስ አንጀለስ ከተማም ሃምሌ 22 ቀን በሎስ አንጀለስ የኢትዮጵያውያን ቀን ሆኖ እንዲከበር ውሳኔ አሳልፏል።(ኤፍቢሲ)