የትግራይ ክልላዊ መንግሥት በጣና በለስ የስኳር ፕሮጀክት ሠራተኞች ላይ የደረሰውን ጥቃት አወገዘ

የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ጣና በለስ የስኳር ፕሮጀክት ይሰሩ በነበሩ የትግራይ ተወላጆች ላይ የደረሰውን ጥቃት አውግዟል፡፡

የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስትም በድርጊቱ የተሰማውን ሀዘን በመግለፅ፣ ጉዳዩን አጣርቶ አጥፊዎችን ለህግ ለማቅረብ ወደ ስፍራው የአመራርና ባለሙያዎች ቡድን መላኩን አስታውቋል።

በፕሮጀክቱ ይሰሩ በነበሩ የትግራይ ተወላጆች ላይ በደረሰው ጥቃት ሶስት ንጹሐን ዜጎች ለህልፈት መዳረጋቸውን  የትግራይ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች  ቢሮ ትናንት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ ገልጿል፡፡

በአማራ ክልል ጣና በለስ  የስኳር ፕሮጀክት ላይ ይሠሩ በነበሩ የትግራይ ተወላጆች ላይ የደረሰው ጥቃት ህገ መንግስታዊ መብትና የሰዎች ነጻነትን የሚገፋ መሆኑን በመግለጽ አውግዘዋል፡፡

“የሓሳብ ልዩነት ካለ ሰላማዊ በሆነ መንገድ መግለጽ እየተቻለ ዘርን በመለየት የሚደረገው ጥቃት በማንኛውንም መለኪያ ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም “ብለዋል፡፡

የክልሉ መንግስት በዜጎች ላይ የደረሰው ጥቃት መሪር ሀዘን እንደተሰማውና ለሟች ቤተሰቦች መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡

በዜጎች ላይ ጥቃት ያደረሱ ግለሰቦች ወደ ህግ እንዲቀርቡ የፌደራልና የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ  መንግስት ወደ ህግ በማቅረብ አስተማሪ እርምጃ እንዲወስዱ ጠይቀዋል፡፡

የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ወደ አካባቢው ቡድን በመላክ ዝርዝር መረጃ ለማቅረብ ጥረት እንደሚያድርግ ጠቅሷል፡፡

በሌላ በኩል የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት  ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን እንደገለጹት በአማራ ክልል በለስ ስኳር ፕሮጀክት በዜጎች ላይ በደረሰው ጉዳት የክልሉ መንግስት የተሰማውን ሀዘን ይገልጻል ፤ ጉዳዩን አጣርቶ አጥፊዎችን ለህግ ለማቅረብም ወደ ስፍራው የአመራርና ባለሙያዎች ቡድን ልኳል።

በክልሉ ውስጥ የዜጎችን ማንነት መነሻ አድርጎ የሚደርስ ጉዳትም ሆነ ማንኛውም ጥቃት የክልሉ መንግስት አምርሮ እንደሚያወግዝና እንደሚታገለው የቢሮው ኃላፊ አቶ ንጉሱ አስታውቀዋል።