የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ በአንድ ወር ውስጥ ወደ ሀገር ቤት በመግባት ሰላማዊ ትግል እንደሚጀምር አስታወቀ

የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ በአንድ ወር ውስጥ ወደ ሀገር ቤት በመግባት ሰላማዊ ትግል እንደሚጀምር ትናንት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል።

የንቅናቄው ሊቀመበር ዶክተር ብርሀኑ ነጋ፣ አንዳርጋቸው ፅጌና ሌሎች የአመራር አባላት ትናንት በጋራ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፥ ንቅንቄው በአንድ ወር ውስጥ ወደ ሀገር ቤት በመግባት ሰላማዊ ትግል እንደሚጀምር ይፋ አድርጓል።

የአርበኞች ግንቦት 7 ከሌሎች የፓለቲካ ፓርቲዎች ጋር ወይንም በተናጠል ለመንቀሳቀስ ያለውን አቋም በሂደት እንደሚወስን ገልጿል።

ንቅናቄው ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ተዋህዶ አንድ ጠንካራ ፓርቲን ለመፍጠር ከተለያዩ ሀገር አቀፍ ፓርቲዎች ጋር ውይይት የማድረግ ፍላጎት እንዳለውም ነው የገለፀው።

ከዚህ በፊት በሀገሪቱ ውስጥ የተፈጠሩት ችግሮች ሀገሪቱን የመኖር እና ያለመኖር ጥያቄ ውስጥ የከተቱ መሆኗቸውን የገለፀ ሲሆን፥ በአሁን ወቅት በሀገሪቱ ያለው ለውጥ የመሸነፍና የማሸነፍ ሳይሆን ወደ ዘመናዊ የዴሞክራሲ ስርዓት የመሸጋገሪያ አጋጣሚ መሆኑም በመግለጫው አመላክቷል።

የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ በዜግነት ላይ የተመሰረት ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት እንደሚንቀሳቀስና በማንነት ላይ የተመሰረት ፌዴራሊዝም ሀገሪቱ ላይ አደጋ ፈጥሯል ብሎ እንደሚያመን አመራሮቹ ተናግረዋል።

የንቅናቄው አመራሮች ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር ሀገሪቱ ውስጥ በሚገኙ ተቋማት ነፃነት ላይ በትኩረት መወያየታቸውና ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ነው የገለፁት።

አሁን ላይ ያሉት የሀገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ማን አሸነፈ የሚለው ጉዳይ ሳይሆን በየጊዜው የሚመጡ ለውጦችን የሚያስተናግድ ዴሞክራሲያዊት ሀገር የመገንባት ጉዳይ ሊያሳስባቸው እንደሚገባ ነው የገለጸው።

በዚህ ወቅት በሀገሪቱ እየታየ ያለው ለውጥ እንዳይቀለበስ ከሌሎች የለውጥ ሀይሎችና ከመንግስት የለውጡ ደጋፊዎች ጋር የመተባበር ፍላጎቱንም አስታውቋል።

የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተለያዩ አመለካከቶች እንደሚኖሯቸው ቢታወቅም ልዩነቶችን በሰለጠነ መንገድ በማስተናገድ ለሀገራዊ ዴሞክራሲ ግንባታ መስራት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።

በመግለጫቸው በሀገሪቱ ውስጥ እየታዩ ያሉ ለውጦች እንዳያመልጡ ሁሉም ኢትዮጵያውያን በትኩረት መንቀሳቀስ እንደሚገባውው አሳስበዋል።

ይህን ለውጥ ከዳር ለማድረስና በሀገሪቱ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለማስፈን የሚያጋጥሙ አደጋዎችን በመጋፈጥ እንደሚንቀሳቀስ ንቅናቄው አስረድቷል።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተመራው ልኡክ ጋር የአርበኞች ንቅናቄው ቡድን ባደረገው ውይይት አሁን ላይ በሀገር ውስጥ የታሰሩ የንቅናቄው አባለት ካሉ ለማስፈታት የሚችልበት ስምምነት ላይ መድረሱንም አስረድቷል።(ኤፍቢሲ)