በሰበታ ከተማ የመልካም አስተዳደር ችግርን ለመፍታት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ ሥርዓት እየተዘረጋ ነው

በሰበታ  ከተማ  የመልካም አስተዳደር ችግርን ለመፍታት የሚያስችል በዘመናዊ ቴክኖሎጂ   የተደገፈ ሥርዓት እየተዘረጋ መሆኑን  የሰበታ  ከተማ  አስተዳደር አስታወቀ ።

የሰበታ ከንቲባ አቶ ለገሰ ነግዎ በተለይ ለዋልታ እንደገለጹት የሰበታ ከተማ የሚታየውን  የአገልግሎት አሠጣጥና የመልካም አስተዳደር ችግር ለመፍታት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ የአሠራር ሥርዓት እየተዘረጋ መሆኑም ተገልጿል፡፡

የሰበታ ከተማ ነዋሪዎች ለዋልታ እንደገለጹት  ከጊዜ  ወደ ጊዜ  ነዋሪዎች  ፍትሃዊ አገልግሎት  ለማግኘት  ጥያቄ  ቢያነሱም  ፍትሃዊ  ምላሽ  እያገኙ  እንዳልሆነ  ገልጸዋል ።  

የሰበታ ከንቲባ አቶ ለገሰ በበኩላቸው  ከህዝብ  ቁጥር መጨመር ጋር በተያያዘ  እያደገ  የመጣውን  የአገልግሎት  ፍላጎትን ለማስተናገድም የመዋቅር እና የአደረጃጀት ለውጥ ለማድረግ ቅድመ ዝግጅቶች   መጠናቀቃቸውን  አስታውቀዋል ።

በሰበታ ከተማ ለህብረተሰቡ ፈጣንና ተደራሽ አገልግሎትን ለመሥጠትም በ5 ክፍለ ከተማዎችና በ16 ቀበሌዎች በአዲስ መልክ ለማደራጀትና የማዋቀር ቅድመ ዝግጅቶች ተጠናቀዋል  ብለዋል ከንቲባው ።

በዘንድሮ ዓመት በመሬት አስተዳደር የአገልግሎት ዘርፍ  የሚታየውን የመልካም አስተዳደር ችግርም    ለመፍታትም  ከ 6ሺህ በላይ  በሚሆኑ አርሶ አደሮች ነባር  ባለይዞታዎችን  ካርታ  ለመሥራት ወደ ተግባር መገባቱን ከንቲባው ገልጸዋል ።

በሰበታ ከተማ ከ3መቶ 50 ሺ በላይ ነዋሪዎች ያሏትና አስር ቀበሌዎች የነበራት ሲሆን ለእነዚህ ነዋሪዎች የመሬት አስተዳደር እና ሌሎችም የከተማ አስተዳደር አገልግሎቶች ምላሽ የሚሠጠው በአንድ ቢሮ ብቻ ነበር፡፡