እየተገነባ ያለውን የፍቅር ድልድይ ከዳር ለማድረስ ሁሉም ኃላፊነቱን እንዲወጣ ተጠየቀ

በአገሪቱ እየተገነባ ያለውን የፍቅር ድልድይ ከዳር ለማድረስ ሁሉም ኃላፊነቱን እንዲወጣ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ጠየቀ።

ጽህፈት ቤቱ በሳምንታዊ የአቋም መግለጫው እንዳመለከተው በውጭ የሚኖሩ ወገኖች የተጀመረውን የይቅርታ ፣ የፍቅር፣ የአንድነት እና የመደመር ጉዞ በመምረጥ ለልዩነት ግንቡ መፍረስ እና ለአዲሱ የፍቅር ድልድይ መገንባት ላበረከቱት አስተዋጽኦ መንግሥት ምስጋናውን አቅርቧል።

በውጭ አገሮች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለሰላም፣ ለአንድነት፣ ለሁለንተናዊ ልማት እና ብልጽግና ያሳዩትን ቁርጠኝነት ወደ ተግባር በመለወጥ እውቀታቸውን እና ገንዘባቸውን ለአገር ግንባታ ለማዋል እንዲረባረቡ መንግስት ጥሪውን አቅርቧል።

የኃይማኖት ተቋማት፣ የሲቪክ ማኅበራትና የፖለቲካ ኃይሎች፣ የኃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራን፣ ወጣቶች እና ሴቶች፣ አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች በአጠቃላይ መላው ህዝብ መገንባት የተጀመረውን የፍቅር ድልድይ ከዳር ለማድረስ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ተጠይቋል። (ኢዜአ)

የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ከኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የተሰጠ የአቋም መግለጫ

 

እየገነባነው ያለውን የፍቅር ድልድይ ከዳር ለማድረስ ሁሉም የጋራ ሃላፊነቱን ይወጣ

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሰሞኑን በሰሜን አሜሪካ ካካሄዱት ጉብኚት ለመረዳት እንደተቻለው በመላው ዓለም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ያለፈውን የጥላቻ እና የቁርሾ ዘመን ወደጎን በመተው በፍቅር እጅ ለእጅ ተያይዘው ለተሻለች አገር ግንባታ በጋራ መሰለፋቸውን አረጋግጠዋል፡፡ 

ኢትዮጵያውያኑ እና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ መንግሥት ያቀረበላቸውን ጥሪ በመቀበል በጋራ ለመስራት እና የአገራችንን ሁለንተናዊ እድገት ለማረጋገጥ ቁርጠኛ መሆናቸውን ያረጋገጡልን በሃሳብም፣ በተግባርም መሆኑም ሌላው ታላቁ ቁም ነገር ነው።

ለ26 ዓመታት ተከፋፍለው የነበሩት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሲኖዶሶች እርቀ ሰላምን ከመፍጠር ባለፈ አራተኛው ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዮስ ወደ አገራቸው ኢትዮጵያ ተመልሰው በይፋ ሥራቸውን ጀምረዋል።

ኢትዮጵያውያኑ እና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ ከማኪያቶ ቀንሰው በቀን አንድ ዶላር በዲያስፖራ ትረስት ፈንድ በኩል ለአገራቸው ልማት እንዲያውሉ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ያቀረቡላቸውን ጥሪ ተቀብለው ወደ ተግባር ገብተዋል። ከተጠየቁትም በላይ ለመስጠት ቁርጠኝነታቸውን አረጋግጠዋል።

ልዩ ልዩ የፖለቲካ ድርጅቶች እና የመብት ተሟጋቾችም የይቅርታ፣ የፍቅር፣ የአንድነት እና የመደመር ጉዞውን በመቀላቀል ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ እድገትና ብልጽግና በጋራ ለመስራት መወሰናቸውን ከማብሰራቸውም በላይ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ገብተዋል። የአርበኞች ግንቦት ሰባት አመራሮች እንዲሁም በመንግሥት ላይ ሲካሄድ የቆየውን የተቃውሞ ትግል በግንባር ቀደምትነት በመምራት የሚታወቁ ተቋማትና ግለሰቦች በቅርቡ ወደ አገራቸው ኢትዮጵያ ለመመለስ እና የበኩላቸውን በጎ አስተዋጽኦ ለማድረግ በዝግጅት ላይ ይገኛሉ።

በውጭ አገር የሚኖሩት እነዚህ ወገኖቻችን ያለፈውን ቂም እና ቁርሾ ወደጎን በመተው ለአገራችን ሁለንተናዊ ዕድገት እና ብልጽግና በጋራ ለመስራት ያሳዩት ቁርጠኝነት እኛ ኢትዮጵያውያን ከመለያየት እና ከመከፋፈል ወጥተን በፍቅር፣ በአንድነት እና በመደመር መርህ የተያያዝነው አገራዊ የለውጥ ጉዞ አገራችን ኢትዮጵያን ከድህነት ለማላቀቅ እና ወደተሻለ ብልጽግና የሚያሸጋግራት መሆኑን ከወዲሁ ያመላከተን ነው፡፡ 

የዋሽንግተን ዲሲ እና የሎስ አንጀለስ ከተሞች ከንቲባዎች ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የገቡበት ዕለት በየዓመቱ የኢትዮጵያውያን ቀን ተብሎ በሁለቱ ከተሞች እንዲከበሩ መወሰናቸውም የጀመርነውን የፍቅር እና የመደመር ጉዞ ጉልበት የሚያመላክት ነው።

በመሆኑም በውጭ የሚኖሩት ወገኖቻችን የተያያዝነውን የይቅርታ፣ የፍቅር፣ የአንድነት እና የመደመር ጉዞ በመምረጥ ለልዩነት ግንቡ መፍረስ እና ለአዲሱ የፍቅር ድልድይ መገንባት ላበረከቱት አስተዋጽኦ መንግሥት በዚህ አጋጣሚ ምስጋናውን በድጋሚ ለማቅረብ ይወዳል።

ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው በኢትዮጵያውያን መካከል ለዓመታት ገንግኖ የቆዬው እና አይደፈሬ ይመስል የነበረው የልዩነት ግንብ በይቅርታና በፍቅር ተንኮታኩቶ መፍረሱን ብቻ ሳይሆን በእሱ ምትክ ለወደፊቷ ኢትዮጵያ መጻኢ እድል መሳካት ወሳኝ የሆነው የፍቅር እና የአንድነት ድልድይ መገንባት መጀመሩን ነው።

በመሆኑም ለወደፊቷ ኢትዮጵያ መፃኢ ዕድል መቃናት ወሳኝ የሆነውን ይህንኑ የፍቅር ድልድይ ግንባታ በፀና መሠረት ላይ ማቆም እና በዘላቂነት ማስቀጠል ይጠይቃል። ይህም የህዝባችንን የጋራ ጥረት እና  ሃላፊነት የሚጠይቅ ነው። ከዚህ አንጻር በውጭ አገራት  የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለሰላም፣ ለአንድነት፣ ለሁለንተናዊ ልማት እና ብልጽግና ያሳዩትን ቁርጠኝነት ወደ ተግባር በመለወጥ እውቀታቸውን እና ገንዘባቸውን ለአገር ግንባታ ለማዋል እንዲረባረቡ መንግስት ጥሪውን ያቀርባል።

በተመሳሳይ፣ የኃይማኖት ተቋማት፣ የሲቪክ ማኅበራትና የፖለቲካ ኃይሎች፣ የኃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራን፣ የከተማ ነዋሪዎች፣ ወጣቶች እና ሴቶች፣ አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች በአጠቃላይ መላው ህዝባችን መገንባት የተጀመረውን የፍቅር ድልድይ እና የተያያዝነውን አገራዊ የለውጥ ጉዞ በጋራ የመጠበቅና የመንከባከብ፣ ብሎም ከዳር የማድረስ የጋራ ሃላፊነት እንዳለብን ተገንዝበን ሃላፊነታችንን እንድንወጣ መንግሥት ጥሪውን ያቀርባል፡፡