የሚያዋጣን በመከባበር ላይ የተመሰረተች ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ አገር በትብብር መገንባት ነው – ጃዋር መሐመድ

ከአሁን በኋላ አዋጪው መንገድ በመከባበር ላይ የተመሰረተች ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ አገር በመተባበር መገንባት እንደሆነ የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ (OMN) መስራች እና አክቲቪስት ጃዋር መሐመድ ገለጸ።

ጃዋር መሐመድና ፕሮፌሰር እስቄል ገቢሳና ሌሎች ኢትዮጵያውያን ትናንት ማለዳ ላይ አዲስ አበባ ገብተዋል።

የኦህዴድ የጽህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ፣ የፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘይኑ ጀማልና በርካታ ወጣቶች ቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ተገኝተው አቀባበል አድርገዋል።

ጃዋር ከ13 አመት በፊት በትምህርት ምክንያት አገሩን ለቆ ወደ አሜሪካ አቅንቶ ነበር። 

በአሜሪካን በነበረው ቆይታ የፖለቲካ አክቲቪስት ሆኖ በአገር ጉዳይ ላይ ማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም  ሲንቀሳቀስ እንደነበር ይታወቃል ።

በዚህ የፖለቲካ አመለካከቱ ምክንያት በኢትዮጵያ መንግስት ክስ ተመስርቶበት እንደነበር ይታወሳል።

ኦ ኤም ኤን እና ጃዋር መሐመድ ላይ ተመስርቶ የነበረው ክስ በቅርብ ጊዜ በተደረገው ይቅርታ ተነስቷል።

በመሆኑም ጃዋር አገር ውስጥ ሆኖ በሙያው ለማገልገል  ወደ አገር ቤት ተመልሷል።

ከጋዜጠኞች ጋር በነበረው ቆይታም ”ወዲህ ማዶና ወዲያ ማዶ ሆኖ መወቃቀስ፣ መፈራረጅና መጣላት እንዲያበቃ ያደረገ” ለውጥ በአገሪቱ መምጣቱ እንዳስደሰተው ተናግሯል።

ለለውጡ መሪዎችና ተዋናዮችም ምስጋና ያቀረበው ጃዋር ልዩነቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ መፍታት አገርና ህዝብን ለማሳደግ የተሻለ አማራጭ መሆኑን ጠቁሟል።

በኢትዮጵያ ከእንግዲህ የሚያዋጣው በመከባበር ላይ የተመሠረተች ሰላማዊ አገር በትብብር መገንባት በመሆኑ ሁሉም ለዚህ በጋራ እንዲሰራ ጥሪ አቅርቧል።

አሁን ያለው ሁኔታ በሙያው አገሩን ለማገልገል ምቹ መሆኑን በመግለጽ ለዚህም መዘጋጀቱን አክሏል።

በስፍራው የተገኙ  የኦህዴድ የጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው ”እነዚህ ሰዎች ወደ አገራቸው መመለሳቸው ትናንት የነበረው የአገሪቱ የፖሊቲካ ሁኔታ መቀየሩን ማሳያ ነው” ብለዋል።

ከአመታት ቆይታ በኋላ በአገሪቱ በመጣው ለውጥ ወደአገራቸው የመጡትን ሰዎች ‘እንኳን ደህና መጣችሁ’ ብለዋቸዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጥሪን ተከትሎ ለበርካታ አመታት ከአገር ወጥተው የቆዩ ፖለቲከኞች፣ የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም መቀመጫቸውን በውጭ አገር ያደረጉ የፖሊቲካ ፓርቲዎች ወደ አገር በመመለስ ላይ ናቸው።(ኢዜአ)