ሼህ ሰኢድ አህመድ ከ23 አመታት የስደት ቆይታ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ

በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ 23 አመታትን በስደት ያሳለፉት የኢትዮጵያ ሙስሊም ወጣቶች ማህበር መስራችና ሊቀመንበር የነበሩት የሃይማኖት አባት ሼህ ሰኢድ አህመድ ሙስጠፋ በተፈጠረው መረጋጋት ምክንያትም ዛሬ ወደ አገራቸው ገብተዋል።

ሼህ ሰኢድ 23 አመት በፊት ነበር ወደ ሳዑዲ አረቢያ የተሰደዱት።

ለስደት ከመዳረጋቸው በፊት የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የዳዕዋና የፈትዋ ኮሚቴ አባል፣ የኢትዮጵያ ቅዱስ ቁርዓን ማህበር አባል የነበሩ ናቸው።

በአሁኑ ወቅትም በሳዑዲ አረቢያ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች አንድነት ማህበር የበላይ ጠባቂ ናቸው።

ሼህ ሰኢድ ከአመታት የስደት ቆይታ በኋላ ዛሬ ቦሌ ዓለም ዓቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት በዚህ ሁኔታ በክብር ወደ አገር ቤት መመለስ ልዩ ስሜት አለው።

ከዚህ በኋላም ባላቸው እውቀትና ባካበቱት ልምድ አገራቸውንና እምነታቸውን ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ሼህ ሰኢድ አዲስ አበባ ሲገቡ የሀይማኖቱ ተከታይ ወጣቶችና አባቶች በቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ተገኝተው አቀባበል አድርገውላቸዋል።(ኢዜአ)