በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁና በርዕሰ መስተዳድር ለማ መገርሳ የሚመራ ልዑክ ወደ አስመራ አቀና

በኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ እና የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ የሚመራው ልዑክ መቀመጫውን ኤርትራ በማድረግ በአቶ ዳውድ ኢብሳ ከሚመራው የኦሮሞ ነጻ አውጪ ግንባር ጋር ለመወያየት ወደ አስመራ አቅንተዋል፡፡

ጉዞውን አስመልክቶም የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

ልዑኩ ዛሬ ጠዋት ወደ አስመራ ያቀና ሲሆን ከሰዓት በኋላ ውይይት እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡

በሀገሪቱ እየተስተዋሉ የመጡትን የፖሊቲካ ምህዳር የማስፋት እና የዴሞክራሲ ግንባታ ለውጦችን በማስመልከት መቀመጫቸውን ውጭ ሀገር አድርገው የነበሩ የተለያዩ የፖሊቲካ እና የሚዲያ ተቋማት ወደ ሀገር ቤት እየተመለሱ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡

በዚህም መሠረት በአሁኑ ወቅት አስመራ የሚገኘው የኦነግ ክንፍም ወደ ሀገር ቤት መመለሱ በጋራ ለሚደረገው የሀገር ግንባታ ወሳኝነት ያለው መሆኑን የኦሮሚያ ክልል የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ለጋዜጠኞች በሰጡ መግለጫ አስታውቋል፡፡

ሰሞኑን በኢትዮ ሶማሌ ክልል ያገረሸው አለመረጋጋት እና ግጭትን በተመለከተም ግጭቱ እንዳይባባስ እና በሰው ህይወትና ንብረት ላይ አደጋ እንዳይደርስ ሁሉም አካላት በእርጋታ እና ሰከን ባለ መልኩ ሊይዙት እንደሚገባ ዶክተር ነገሪ አሳስበዋል፡፡

በአዋሳኝ አካባቢ የሚገኙ የኢትዮ ሶማሌ እና የኦሮሚያ ክልል ነዋሪዎችም ደህንነታቸው የሚጠበቅ በመሆኑ ህብረተሰቡ በተለመደው አብሮነት ተረጋግተው እንዲቆዩም ጥሪ ቀርቧል፡፡

ሰመኑን በክልሉ የተባባሰው አለመረጋጋት የሁለቱ ክልሎች የሰላም ኮንፌሬንስ ለማካሄድ በሚንቀሳቀሱበት ወቅት በመሆኑ ሰላም የማይፈልጉ አካላት ተግባር መሆኑን በመገንዘብ  በጥንቃቄ ሊያዝ ይገባልም ተብሏል፡፡