ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለሚሰማሩ 1 ሺህ ወጣቶች ገለፃ አደረጉ

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለሚሰማሩ 1 ሺህ ወጣቶች በዛሬው ዕለት ገለጻ አድርገዋል።

የወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ከዛሬ ነሐሴ 1 ቀን እስከ ነሐሴ 15 ቀን 2010 ዓ.ም የሚካሄድ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድም ዛሬ የተጀመረውን የወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በማስመልከት ነው ለተሳታፊዎቹ ገለጻ ያደረጉት።

በዛሬ ይፋ በተደረገው የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ላይ ከሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ 1 ሺህ ተመራቂ ወጣቶች ተሳታፊዎች ናቸው።

ወጣቶቹ ከሚኖሩበት ክልል ባለፈ ወደ ሌሎች ክልሎች በመሄድ በተለያዩ ተግባራት ላይ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ይሰጣሉ።

ይህ ወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መካሄድ ሀገራዊ ስሜትንና የህዝብ ለህዝብ ማህበራዊ ትስስርን ያጎለብታል ተብሎ ይጠበቃል።

የበጐ ፈቃድ አገልግሎት ዜጐች በተለይም ወጣቶች ያለማንም አስገዳጅነት ለሚኖሩበት ማህበረሰብ ልማትና ለአካባቢ ደህንነት የራሳቸውን አስተዋጽኦ የሚያደርጉበት ነው።

የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር፣ የሳይንስና ቴክኖሎጅ ሚኒስቴር፣ የትምህርት ሚኒስቴር፣ የአካባቢ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር እና የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ፕሮግራሙን በጋራ ያስተባብሩታል።

ከወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች የበጐ ፈቃድ አገልግሎት ባለፈ በዘንድሮው የወጣቶች የክረምት ወራት የበጐ ፈቃድ አገልግሎት በሀገር አቀፍ ደረጃ 13 ነጥብ 6 ሚሊየን የሚሆኑ ወጣቶች የበጐ ፈቃድ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከአንድ ክልል ወደ ሌላ ክልል በመሄድ ማከናወን ከማህበራዊ ጠቀሜታው ባለፈ፥ ኢትዮጵያዊነትን ከፍ በማድረግ የበለጠ መቀራረብ እና አንድነትን ለመፍጠር እንደሚያስችል መናገራቸው ይታወሳል። (ኤፍቢሲ)