በጅግጅጋ እና አጎራባች ዞን ከተሞች አንፃራዊ ሰላም መሰፈኑን የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር አስታወቀ

በጅግጅጋ ከተማ እና በአጎራባች ዞን ከተሞች በዛሬው እለት አንፃራዊ ሰላም መሰፈኑን የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር አስታውቋል፡፡

ከዋልታ ጋር ቆይታ ያደረጉት በሚኒስትሩ የኢንዶክትርኔሽንና የህዝብ ግንኙነት ዋና ዳይሬክተር ሜጄር ጄነራል መሀመድ ተሰማ የመከላከያ ሰራዊቱ ወደ ጅግጅጋ ከገባ በኋላ አንጻራዊ ሰላም መስፈኑን ገልጸዋል፡፡

በዛሬው ዕለት ዝርፊያም ሆነ የጥይት ድምፅ በከተማዋ አልተሰማም ያሉት ሜጄር ጄነራሉ አንዳንድ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ስራ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡

በከተማዋ የሚገኙ የንግድ ተቋማት ሙሉ በሙሉ ስራ እንዲጀምሩ ከኡጋዞች እና አካባቢ ነዋሪዎች ጋር ውይይት እየተደረገ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ የውሃ፣ መብራትና የመሳሰሉ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ስራ እንዲጀምሩ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

መከላከያ ሰራዊቱ ከፌዴራል ፖሊስ ጋር በመሆን ከጅግጅጋ በተጨማሪ በጎዴ፣ ደጋሀቡር እና ሌሎች የዞን ከተሞች መረጋጋት ለማስፈን እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተፈጠረው ግጭት ወቅት የተፈፀመው ዝርፊያ የማጣራት እና የመለየት ስራ እየተካሄደ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡