የኤርትራ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኡስማን ሳልህ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት አዲስ አበባ ገቡ

የኤርትራው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኡስማን ሳልህ ዛሬ አዲስ አበባ ገቡ።

ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በቆይታቸው ከኢፌዴሪ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ይወያያሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያወጣው መረጃ ያመላክታል።

ጉብኝቱ ዳግም የተጀመረውን የሁለቱን ሃገራት ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ እንደሚያግዝም ታምኖበታል።

ኢትዮጵያና ኤርትራ ለ20 አመታት አቋርጠውት የነበረውን ግንኙነት ዳግም መጀመራቸው ይታወሳል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአስመራ ታሪካዊ የተባለውን የመጀመሪያ ጉብኝት ማድረጋቸዉም ይታወቃል።

በጉብኝታቸው ወቅትም የሁለቱን ሃገራት የንግድና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት የሚያጠናክሩ ስምምነቶችን ተፈራርመዋል።

የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂም በኢትዮጵያ ጉብኝት በማድረግ በአዲስ አበባ የሚገኘውን የኤርትራ ኤምባሲ መርቀው ከፍተዋል።

በቅርቡም የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁና የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ ወደ ኤርትራ በማቅናት ከኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸው የሚታወስ ነው።