የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ አባቶች በጅግጅጋ ከተማና አካባቢዋ የተፈጠረውን ግጭት አወገዙ

የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ አባቶች በኢትዮጵያ ሶማሌ ዋና ከተማ በሆነችው ጅግጅጋ እና አካባቢዋ የተፈጠረውን ግጭት አወገዙ፡፡

በተለያዩ ኃይማኖቶች ህዝቡ ተከባብሮ በሚኖርበት ሀገር ላይ በአሁኑ ሰዓት እየተፈጸመ ያለው ተግባር የሚወገዝ መሆኑን የገለጹት አባቶች በሀገሪቱ ስርዓተ አልበኝነት እና ህገወጥነት እየተንሰራፋ ይገኛል ብለዋል፡፡

ይህ ስርአት አልበኝነት በመቆም በሀገሪቷ ሰላም እና የህግ በላይነት እንዲሰፍን መሰራት እንዳለበትና ሁሉም አካላት የበኩሉን መወጣት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

ወጣቶች ከህገ ወጦች እና ሰላም ከሚያደፈርሱ ተግባራት በመራቅ ለሰላም ዘብ መቆም እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

በተፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት በተለያዩ አካባቢዎች ለተፈናቀሉ ወገኖችም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉም የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ አባቶች ገልጸዋል፡፡