የአፋር መንፈሳዊ አባትና ባህላዊ መሪ ሱልጣን ሐንፍሬ አሊሚራህ አዲስ አበባ ገቡ

በስደት ይኖሩ የነበሩት የአፋር መንፈሳዊ አባትና ባህላዊ መሪ ሱልጣን ሐንፍሬ አሊሚራህ አዲስ አበባ ገቡ።

ሱልጣን ሐንፈሬ ዛሬ ጠዋት ቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትና የአፋር ክልል ፕሬዚዳንት ሼህ ስዩም አወል አቀበባል አድርገውላቸዋል።

ሱልጣን ሐንፈሬ አሊሚህራ በአገሪቱ በመጣው ለውጥ ወደአገራቸው ለመመለስ መብቃት በመቻላቸው ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይና የሥራ አጋሮቻቸው ወደ ስልጣን ከመጡ በዋላ የተመዘገበው ለውጥ እሳቸው ብቻ ሳይሆኑ በውጭ አገር የሚኖሩ በርካታ ዜጎችም ደስተኛ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የአፋር ክልል ፕሬዚዳንት ሼክ ስዩም አወል በበኩላቸው ሱልጣኑ የፖለቲካ ሰው ሳይሆኑ የአፋር አባት በመሆናቸው ወደ አገር መመለሳቸው ለክልሉና ለአገሪቱ ሰላምና ልማት የላቀ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

ለአገሪቱም ሆነ ለክልሉ ልማትና ሰላም መረጋገጥ በቀጣይም ሰፊ ውይይት በማድረግ በትብብር ለመስራት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጠር ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ በአገሪቷ እየተካሄደ ባለው ለውጥ ውስጥ የሱልጣን ሐንፍሬ ወደአገር መመለስ የሚያስደስትና በቀጣይ ለሚሰሩ ስራዎች መሰረት የሚጥል እንደሆነ አመልክተዋል።

በውጭ አገር ለአገሪቷ በጎ የሚያስቡ በርካታ ልምድ፣ አስተሳሰብና ዕውቀት ያላቸው ዜጎች መኖራቸውን ጠቁመው የሱልጣን ሐንፍሬ መምጣት ለሰላም፣ እድገትና ለፖለቲካ ምህዳር መስፋት ወሳኝ ሚና ይጫወታል ሲሉ ተናግረዋል።

መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሹመታቸው ወቅት በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ወደ አገራቸው እንዲገቡ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወቃል።