በሻሸመኔ ከተማ ወንጀል ፈጽመዋል የተባሉ አካላት በቁጥጥር ስር እየዋሉ መሆኑ ተገለፀ

በሻሸመኔ ከተማ ባለፈው እሁድ የኦኤምኤን ስራአስኪያጅና የፖለቲካ ተንታኝ የሆነውን ጃዋር መሐመድ የአቀባበል ሥነስርዓት ላይ ወንጀል ፈጽመዋል የተባሉ አካላት በቁጥጥር ስር እየዋሉ መሆናቸውን የሻሸመኔ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ገለጸ፡፡

ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ በዛሬው ዕለት አራት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን በመምሪያው የምርመራ ክፍል ሃላፊ ኮማንደር ታሪኩ ለገሰ  ለዋልታ አስታውቀዋል፡፡

በተጠርጣሪዎቹ ላይ ተጨባጭ መረጃ የማፈላለግ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ እና ተጨማሪ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል ግብረኃይል ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን ኮማንደር ታሪኩ ገልጸዋል፡፡

ከሻሸመኔ ከተማ ፖሊስ መምሪያ፣ ፍትህ ቢሮ እንዲሁም የምዕራብ አርሲ ዞን ፍትህ ቢሮና ፍትህ መምሪያ፣ የኦሮሚያ ክልል ፍትህ ቢሮና ፖሊስ ኮሚሽን የግብረኃይሉ አባላት ናቸው ተብሏል፡፡