በኢትዮጵያ የተጀመረውን የለውጥ ሂደት እንደሚደግፉ አምባሳደሮች ገለፁ

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የተጀመረው አገራዊ የለውጥ ሂደት የተሳካ እንዲሆን ድጋፍ እንደሚያደርጉ በኢትዮጵያ የነበራቸውን የሥራ ጊዜ ያጠናቀቁ  አምባሳደሮች ገለፁ።

አገሮቻቸውን በመወከል ላለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ የቆዩት የካናዳ፣ ዴንማርክና ቱኒዚያ አምባሳደሮች ይህንን የገለፁት ዛሬ የስንብት ደብዳቤዎቻቸውን ለፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ባቀረቡበት ወቅት ነው።

ተሰናባች አምባሳደሮች በኢትዮጵያ ላለፉት ሶሰት ዓመታት ያገለገሉት የካናዳ አምባሳደር ፍሊፕ ቤከር እና የዴንማርክ አምባሳደር ሜት ታይሰን እንዲሁም ለአምስት ዓመታት በአዲስ አበባ የቆዩት የቱኒዚያ አምባሳደር ሳሃብ ከሃልፈላህ ናቸው።

በብሄራዊ ቤተ-መንግስት በተከናወነው የስንብት ስነ -ርስዓት ላይ አምባሳደሮቹ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ያከናወኑትን ተግባር እና አገሮቻቸው  ከኢትዮጵያ  ጋር ያላቸውን የትብብር ግንኙነት በተመለከተ ከፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ጋር መክረዋል።

ከውይይቱ መልስ ያነጋገርናቸው የካናዳ አምባሳደር ፍሊፕ ቤከር በኢትዮጵያ ቆይታቸው በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን የምጣኔ ኃብትና ፖሊቲካዊ ግንኙነት ለማጠናከር ያከናወኑት ተግባር ውጤታማ እንደነበር ተናግረዋል።

በተለይም በማዕድን እና ሌሎች ልማት ዘርፎች እንዲሁም በፖሊቲካው ረገድ በኢትዮጵያ የተዘረጋውን የፌዴራላዊ ስርዓት ለማጠናከር የሚያስችል ድጋፍ በካናዳ በኩል ሲደረግ መቆየቱን አምባሳደሩ ገልፀዋል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የተጀመረው የለውጥ ሂደት የሚያበረታታ መሆኑን ያመለከቱት አምባሳደር ቤከር ”ይህ የለውጥ ሂደት ከግብ ይደርስ ዘንድ የካናዳ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ይሰጣል” ብለዋል።

በአትዮጵያውያን እንግዳ ተቀባይነትና ሰው ወዳድነት ባህል መማረካቸውንም አምባሳደር ቤከር ጠቅሰዋል።

ተሰናባቹ የቱኒዚያ አምባሳደር ሰሃብ በበኩላቸው በአገራቸውና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ጠንካራ ግንኙነት ቀጣይነት እንዲኖረው፣ የቱኒዚያ ኢንቨስተሮች መዋለ ንዋያቸውን በኢትዮጵያ እንዲያፈሱ የሚሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ጋር ያካሄዱት ውይይትም በዚህ ዙሪያ ላይ ያተኮረ እንደነበር አምባሳደሩ ተናግረዋል።

የፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት የፕሮቶኮልና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አሸብር ጌትነት እንደተናገሩት፤ አምባሳደሮቹ ከፕሬዝዳንቱ ጋር የነበራቸው የምክክር ጊዜ አገሮቹ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸው ግንኙነት ተጠናክሮ የሚቀጥልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነበር።

ከነዚህ መካከልም በንግድና ኢንቨስትመንት ዙሪያ የተጠናከረ የትብብር ግንኙነት እንዲፈጠር በኢትዮጵያ በኩል ከፍተኛ ፍላጎት መኖሩን  ፕሬዝዳንቱ ለአምባሳደሮቹ ገልጸዋል።

አምባሳደሮቹም አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ እያተካሄደ ያለው ለውጥ ለአገሪቱ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም የሚተርፍና በአለም ደረጃም በአብነት የሚጠቀስ በመሆኑ ሁሉም በአወንታ እንደሚመለከተው ለፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።

በመሆኑም አገሮቹ ይህ የለውጥ እንቅስቃሴ ግቡን እንዲመታ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉም ለፕሬዚዳንቱ ቃል ገብተዋል። (ኢዜአ)