ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገራዊ መግባባትና እርቀሰላም ዙሪያ ተወያዩ

ከ43 በላይ የሚሆኑ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተሳተፉበት የሀገራዊ መግባባት እና የእርቀ ሰላም ውይይት መድረክ ዛሬ ተካሂዷል፡፡

ውይይቱ በወቅታዊ የሀገሪቱ የፖለቲካና የዴሞክራሲ እንቅስቃሴ በጋራ መምከርን ዓላማው ያደረገ ሲሆን በሀገሪቱ እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ መሰራት እንደሚገባ በመድረኩ ተጠቁሟል፡፡

አሁን የተገኘው የዴሞክራሲ እና የለውጥ ዕድል መጠቀም እንደሚገባ የተናገሩት የመድረኩ ተሳታፊዎች በሀገሪቱ እየተስተዋለ ያለውን ችግር ለመፍታት የተፎካካሪ ፓርቲዎች አስተዋጽኦ ጉልህ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል፡፡

ለዚህም መፍትሔው የተፎካካሪ ፓርቲዎች ጠንካራ መሆንና ከብዛት ይልቅ ሶስት እና አራት በመሆን መደራጀት እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡

አሁን ያለውን የብሔራዊ መግባባት እና ዕርቅ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ መሰል መድረኮች በስፋት መዘጋጀት አለበት ተብሏል፡፡

ይህንንም ለማድረግ በሚያስችል መልኩ እንደሚሰራ በውይይቱ ተነስቷል፡

እንደ ሀገር የተጀመረውን ለውጥና በየአካባቢው የሚስተዋሉ ችግሮች ለመፍታት መንግስት ብቻውን መስራት እንደሌለበትና ችግሩን ለመፍታት የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ህዝቡ የተቀናጀ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለባቸው ተመልክቷል፡፡ 

በውይይት መድረኩ ላይ ምሁራን፣ የሀይማኖት ተቋማት ተወካዮች፣ የሲቪክ ማህበራትና ሌሎችም አካላት ተሳትፈዋል፡፡