በተጠናቀቀው በጀት አመት ስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራ መሰራቱን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አስታወቀ

በተጠናቀቀው በጀት አመት ስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራዎች እንደተሰሩ የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አስታወቀ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው ሀገሪቱ ከጎረቤት ሀገራት፣ ከመካከለኛው ምስራቅ እና ከምዕራብና ኢሲያ ሀገራት ጋር የተጠናከረ ዲፕሎማሲያዊ ስራዎች በ2010 ዓ.ም እንደተሰሩ አስታውቋል፡፡

ከጎረቤት ሀገራት ጋር የጉብኝት ልውውጦች እንደነበሩ እና በጋራ የመልማት ስምምነቶች የተደረሱበት እንደሆነ የሚኒስትሩ ቃልአቀባይ አቶ መለስ ዓለም በመግለጫቸው ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከራስ አልፎ የጎረቤት ሀገራት ሰላም ከማስከበር ረገድ በሶማሊያ፣ ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን መስራቷንም አንስተዋል፡፡

የአባይ ውሃ አጠቃቀም ረገድም በመሪዎቹ ደረጃ መግባባት ላይ የተደረሰበትና የሀገራቱ ግንኙነት ከግድቡ በላይ መሆኑ የታየበት እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

ከመካከለኛው ምስራቅ፣ ምዕራብ እና ኢሲያ ሀገራት ጋርም በኢኮኖሚ እና ፖለቲካው ዘርፍ ስኬታማ ስራዎች እንደተሰሩ የተናገሩት ቃል አቀባዩ ይህም የአገሪቱ የውጭ ግንኙነት ያለበትን ደረጃ ያሳየ እንደነበረ ገልጸዋል፡፡

ከዳያስፖራ ማህበረሰብ ጋር ያለው ግንኙነት የተጠናከረበትና ከዚህ በፊት የነበሩ የጥላቻ ግንብ በማፍረስ የዲፕሎማሲው ስራ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ መሆኑ የታየበት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተገኙ ስኬቶችን ለማስቀጠል መዘጋጀቱንና ለዚሁም በ2011 በጀት አመት በሀገር ውስጥ ያለውን ሰላም፣ ከአጋር ሀገራት ጋር ያለውን ግንኙነት ፍላጎትና ተቀባይነት፣ ውጭ ያሉ ኢትዮጵያዊያን አስተዋጽኦ መጠቀም ለዘርፉ ምቹ ሁኔታዎችን እንደምፈጥርም አቶ መለስ አለም ገልጸዋል፡፡