ህወሓት በምሁራን የተደረጉ ጥናቶች ወደ ተግባር ለመቀየር አቅጣጫ አስቀመጠ

የትግራይ ክልል ልማትና የመልካም አስተዳደር ግንባታ ወደተሻለ ደረጃ ለማሸጋጋር በምሁራን የተደረጉ ጥናቶች ወደ ተግባር ለመቀየር ህወሓት አቅጠጫ ማስቀመጡን አስታወቀ፡፡

የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ከነሐሴ 18 እስከ 2ዐ/2ዐ1ዐ ያካሄደውን መደበኛ ስብሰባ አጠናቋል፡፡ 

ማዕከላዊ ኮሚቴው በ3 ቀናት ስብሰባው የክልሉን እና የሃገሪቱን ሁኔታዎች በማስመልከት ሰፊ ውይይት ያካሄደ ሲሆን በክልሉ ቀጣይ የልማት፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ አጀንዳዎች ላይ በጥልቀት መክሯል፡፡

የልማትና የመልካም አስተዳደር እንዲሁም ዴሞክራሲን የማስፋት ጉዳዮች ማዕከላዊ ኮሚቴው የመከረባቸው ቁልፍ አጀንዳዎች ሲሆኑ በቅርቡ በሙሁራን የተደረጉ ጥናቶች የደረሱበትን ደረጃ በመገምገም የአፈፃፀማቸውን ሂደት አስቀምጧል፡፡

የኢትዮ-ኤርትራ የሰላም ሂደትን በመደገፍ እንዲሁም በህገ-መንግሥቱና ፌደራላዊ ስርአቱ ላይ የተጋረጡ ስጋቶችን በማስመልከት በክልሉ የተደረገው ህዝባዊ ሰልፍ ላይ ህዝቡ ላሳየው ብስለትና ፅናት  ማዕከላዊ ኮሚቴው  አድንቋል፡፡

አሁንም ቢሆንም በማይናወጥ አቋማችን ለክልሉ ሰላምና ደህንነት፣ ለህገመንግሥቱና ፌደራላዊ ሥርዓቱ ሁሉም እንዲቆምም ጥሪውን ያቀርባል፡፡

አሁን የምንገኝበት የትግል ምዕራፍ ከመቼውም ጊዜ በላይ የአመራሩ፣ የአባሉና የህዝቡ አንድነት የሚጠይቅ መሆኑን የገለፀው ማዕከላዊ ኮሚቴው አሁንም ቢሆን በአንድነታችን ላይ በሚደረጉ ዘመቻዎችን በፅናት እንድንመክታቸው ሲል ጥሪውን ያቀርባል፡፡

መሪው ድርጅትም ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በመርህ ላይ የተመረኮዘ አንድነትን በማጠናከር ለህዝቡ ሰላምና ልማት አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡

የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ቀጣዩን ጉባኤ በተመለከተ የመከረ ሲሆን ጉባዔው አሁን ያለው የትግል መድረክ በብቃት በመምራት ወደተሻለ ምዕራፍ ሊደርስ በሚችልበት መንገድ ጠንክሮ የሚወጣበት ሊሆን እንደሚገባ አስምሯበታል፡፡

ጉባኤው ፍፁም ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንደሚካሄድ እና አንድነታችንን ጠብቀው በክልልም ሆነ በሃገር አቀፍ ደረጃ የሚያጋጥሙንን ተግዳሮቶች ለመግታት በሚያስችለን ቁመና ተጠናክረን የምንወጣበት ሊሆን እንደሚገባም ማዕከላዊ ኮሚቴው መወስኗል፡፡

ለጉባዔው መሳካት መሪ ድርጅቱ ከአባላቱ ጋር በመሆን ይሰራል ያለው ማዕከላዊ ኮሚቴው ፣ በመጨረሻም በክልሉ የሚደረጉ የተደራጁና ያልተደራጁ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ለዴሞክራሲ መዳበርና የህዝቦችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድ ያላቸውን ሚና እንደሚረዳ ይገልፃል፡፡

በተጨማሪም  ህገ- መንግሥቱን መሠረት በማድረግ የህዝብን ተጠቃሚነት በማስቀደም ከሚሰሩ ድርጅቶች ጋር አብሮ ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን በድጋሚ ይገልፃል፡፡

የህ.ወ.ሓ.ት ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽ/ቤት