የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የቀድሞ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዲ ሙሐመድ ዑመር ፍርድ ቤት ቀረቡ

በዛሬው እለት አቶ አብዲ መሐመድ ዑመርን ጨምሮ ሌሎች ሰባት ተጠርጣዎች በፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ተረኛ 1ኛ ወንጀል ችሎት ነው የቀረቡት።

የፌደራል ፖሊስ መርማሪ አቶ አብዲ እና ሌሎች ተጠርጣሪዎች በክልሉ በተለይም በጅግጅጋ እና አካባቢው በተፈፀመው የሰብአዊ መብት ጥሰት በዋና ተዋናይነት እጃቸው አለበት ተብሎ በመጠርጠራቸው ፍርድ ቤት የቀረቡት ናቸው ብሏል።

በአሁኑ ወቅትም አጠቃላይ ምርመራ ለማካሄድ መርማሪ ፖሊስ የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ፍርድ ቤትን እየጠየቀ ነው።

አቶ አብዲ በፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ተረኛ 1ኛ የወንጀል ችሎት ቀርበው የነበረ ቢሆንም፥ በአሁኑ ወቅት ወደ ፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተወስደዋል።

አቶ አብዲ ከትናንት በስቲያ ሰኞ በአዲስ አበባ ከተማ አትላስ አካባቢ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው በቁጥጥር ስር መዋላቸው የሚታወስ ነው።

በቁጥጥር ስር በዋሉበት ወቅትም በመኖሪያ ቤታቸው የጦር መሳሪያ ተገኝቶባቸዋል።

የሶማሌ ክልል ምክር ቤትም ባለፈው ዕሁድ ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ የአቶ አብዲ መሐመድ ዑመርን ጨምሮ የ7 የክልሉ የቀድሞ የምክር ቤት አባላትን ያለመከሰስ መብት ማንሳቱ ይታወሳል።(ኤፍቢሲ)