ፍርድ ቤቱ የአቶ አብዲ መሃመድን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ አደረገ

ፍርድ ቤቱ በዛሬው ዕለት ውሎው የቀድሞ የኢትዮጵያ  ሶማሌ ክልል  ፕሬዚደንት አቶ አብዲ መሃመድን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ  ለፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ  ጊዜ  ሠጥቷል ።

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በልደታ ምድብ 19ኛው የወንጀል ችሎት ተከሳሾች የሆኑት አቶ አብዲ፣ ወይዘሮ ሩሃማ መሐመድና አቶ አብዱ ራዛቅ ሳህኒ ያቀረቡት የዋስትና መብት ጥያቄ ፍርድ ቤቱ ውድቅ አድርጎታል።

ፍርድ ቤቱ በዋለው ችሎት ፖሊስ ያቀረበውን የ14 ተጨማሪ የምርመራ  ጊዜም ፈቅዷል ።

ፍርድ ቤቱ የቀድሞ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ፕሬዚደንትን ጨምሮ ሁለት ተከሳሾች በዛሬው ዕለት በዋለው ችሎት ኢጎ የተባለ ህገ ወጥ ቡድን በማደራጀት የፀጥታ ችግር በመፍጠር   የዜጎች መብትና ንብረት በማውደም ተከሰዋል ።  

ሦስቱም ተከሳሾች በችሎቱ ቀርበው በአሥር  ቤት  ያላቸው  አያያዝ  የተሻለ  እንዳልሆነና  ለጤናቸው  ምቹ  እንዳልሆነ   ተናግረው ፍርድ ቤቱ ይህ እንዲስተካከል ለፌደራል  ፖሊስ  ትዕዛዝ  ሠጥቷል  ።

በተጨማሪም  አቶ ሱልጣን አህመድ የተባለው ተከሳሽ  የተያዙት  በስም  መመሳሰል  ምክንያት  በመሆኑ   መለቀቃቸውን የፌደራል  ፖሊስ አስታውቋል  ።

በፍርድ ቤቱ ውሎ የፌደራል ፖሊስ በዛሬው  ዕለት የክልሉ  ፖሊስ  ኮሚሽን ኮሚሽነር በነበሩት  አቶ  ፌርሃን  ጣኢር  ቤርኬሌ  ላይ  አዲስ  የክስ  ፋይል  እንዲከፈት ማድረጉን ገልጿል ።

ኮሚሽነሩ ከግብር አበሮቹ  ጋር  በመሆን ኢጎ  የተባለው  የህገ ወጥ  ቡድን  ህገ ወጥ የጦር  መሣሪያዎችን  እንዲታጠቁ  በማድረግ  በክልሉ  ከሐምሌ 26 እስከ 29  ድረስ  በተፈጠረው  ሁከት የአካል ጉዳት በማድረስ ተጠርጣሪ በመሆን ነው  በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተገልጿል ።

በዛሬው ዕለት ችሎቱ  የቀረቡት  አቶ  ፈርሃን ጣኢር  በበኩላቸው  የስኳር በሽታ  ያለባቸው እንደሆነና  ለጤና  ችግራቸው  ድጋፍ  የሚያደርግ  ቤተሰብ በአዲስ አበባ የሌላቸው በመሆኑ ቀነ ቀጠሮው  እንዲያጥርላቸው  የጠየቁ  ቢሆንም  ፍርድ ቤቱ  ውድቅ አድርጎታል  ።

ሁሉም  ተከሳሾች  ክሳቸው   ለመስከረም  4  ፤ 2011 ዓም  ቀርበው ክሳቸው እንዲታይ  ፍርድ ቤቱ ተለዋጭ ቀጠሮ ሠጥቷል   ።