ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ከአርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነ ጋር ተወያዩ

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ከአርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነ ጋር በጽህፈት ቤታቸዉ ተገናኝተው ተወያይተዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ ኢትዮጵያ ውስጥ በተፈጠረዉ መልካም የፖለቲካ ድባብ ታማኝ እና ሎሎች ኢትዮጵያውያን ወደ ሃገራቸዉ በመመለስ ለሀገራቸው እድገት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ለማበርከት በመምጣታቸዉ አድናቆታቸዉን መግለጻቸውን በጽህፈት ቤቱ የኮሙኒኬሽንና ፕሮቶኮል ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ አሸብር ጌትነት ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም በሃገሪቱ ልማትና እድገት ለሚያበረክቱት አስተዋፅኦ መንግስት አስፈላጊዉን ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃልመግባታቸውን አቶ አሸብር ገልጸዋል፡፡

ከፕሬዚዳንት ጋር  በተደረገው  ዉይይትም በሃገሪቱ የተጀመረዉን ለዉጥ ለማስቀጠል የበኩላቸዉን ለመወጣት ዝግጁ እንደሆኑና በመንግስት በኩልም ጊዜ ሳይሰጥ ስራዎች መሬት ላይ ተግባራዊ መደረግ እንዳለበት አርቲስት፣ አክቲቪስትና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ታማኝ በየነ ከውይይት በኋላ ለጋዜጠኖች በሰጠዉ መግለጫ ተናግሯል፡፡ 

ወጣቱ ያለዉ ተነሳሽነት የሚያስደስት ቢሆንም በሃገሪቱ በአንዳንድ አካባቢዎች በነበረዉ ውጥረት ከፍትህ ተቋማት ዉጪ ዳኝነት የመስጠት አዝማሚያዎች የተጀመረዉን የለዉጥ ጉዞ የሚያደናቅፍ በመሆኑ ሁሉም ዜጋ ሊከላከለዉ እንደሚገባ ታማኝ ገልጸዋል፡፡

በውጭ የሚኖረዉን ኢትዮጲያውያንን  በማስተባበር የተጀመረውን የዲያስፖራ ትረስት ፈንድ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሰራ እንደሆነና ዲያስፖራዉ በፋይናንስም ሆነ በሙያዉ ለሃገሩ ድርሻውን ለማበርከት ከፍተኛ ተነሳሽነት እንዳለዉ አርቲስትና አክቲቪስቱ ተናግሯል፡፡