ኢትዮጵያ ከአውሮፓ፣ አሜሪካ፣ እስያና ኦሽንያ አገራት ጋር ለስትራቴጂያዊ ትብብር ትሰራለች

ኢትዮጵያ ከአውሮፓ፣ አሜሪካ፣ እስያና ኦሽንያ አገራት ጋር ለስትራቴጂያዊ ትብብር እንደምትሠራ  የውጭ  ጉዳይ  ሚንስቴር አስታወቀ ።

ኢትዮጵያ ከአውሮፓ፣ አሜሪካ፣ እስያና ኦሽንያ አገሮች እንዲሁም ከአለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር ያለው ግንኙት ወደ ስትራቴጂያዊ አጋርነት እንዲያድግ በጥናት ላይ የተመሠረተ ስራ እያካሄደች ነው።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ ትናንት በጽህፈት ቤታቸው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ሚኒስቴሩ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የዲፕሎማሲ ጥረቱን በበቂ ጥናት ላይ ተመስርቶ በማከናወኑ ውጤታማ መሆን ችሏል ።

በተጠናቀቀው በጀት አመት ከ13 አገራት ጋር የፖለቲካ ምክክሮች፣ የጋራ ኮሚሽን ስብሰባዎችና ከፍተኛ ውጤት ያስገኙ የከፍተኛ አመራሮች የስራ ጉብኝት ልውውጦችን ማድረግ እንደተቻለም አብራርተዋል።

ይህንንም ተከትሎ ከአገራት ጋር ዘጠኝ አዲስ ስምምነቶችን መፈራረም የተቻለ ሲሆን ከአውሮፓ፣ አሜሪካ፣ ኤዥያና ኦሽንያ፣ አውስትራሊያ አገሮችና ከአለምዓቀፍ ተቋማት ብቻ ከ2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር በላይ አዲስ የልማት ትብብር ድጋፍ ማስገኘት ተችሏል።

ሚኒስትር ዴኤታው አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ኩባ፣ ብራዚልና ህንድ, ካዛኪስታን፣ ላቲቪያ እና ፖላንድን ጨምሮ ከዘጠኝ አገራት ጋር የስትራቴጂክ ግንኙነት ለመመስረት የሚያስችሉ ሰፊ ጥናቶች ተዘጋጅተው ምክክር እየተደረገባቸው መሆኑን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ዲፕሎማሲውን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ በበጀት ዓመቱ የአገራችንን የውክልና አድማስ የማስፋት እርምጃዎችም የተወሰዱ ሲሆን በኔዘርላንድስ አዲስ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተከፍቷል።

በአሜሪካ፣ ካናዳ፣ ጣልያን፣ ፈረንሳይ፣ ሲንጋፖርና አውስትራሊያን ጨምሮ ከ10 በላይ ተጨማሪ የክብር ቆንስላ ጽህፈት ቤቶች እንዲከፈቱ አድርጓል።(ምንጭ: የውጭ ጉዳይ ሚኒሰቴር ቃልአቀባይ ጽህፈት ቤት)