የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ ሊቋቋም ነው

የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ ሊቋቋም መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ መለስ አለም ዛሬ በሰጡት መግለጫ፥ ኤጀንሲው በውጭ ሀገር የሚኖሩ ዜጎችን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ የበለጠ ለማስተባበር፣ ለማቀናጀት፣ መብትና ተጠቃሚነትን ለማስከበር እንደሚያስችል ገልፀዋል።

አሁን ላይ በሃገሪቱ የፓለቲካና የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች እየተደረጉ ሲሆን፥ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክትር አብይ አህመድን ጥሪ ተከትሎ ከኢትዮጵያ ርቀው በውጭ ሀገር የቆዩ በርካታ ዜጎች ወደ ሀገራቸው አየተመለሱ መሆኑንም አስረድተዋል።

እነዚህ ዜጎች በተለያዩ ዘርፎች አገራቸውን ለማገልገል ዝግጁነታቸውን እየገለጹ ሲሆን፥ ለዚህም መንግስት የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ ለማቋቋም በሂደት ላይ መሆኑን ነው አቶ መለስ በመግለጫቸው የተናገሩት።

በዜጎች መካከል የፓለቲካም ይሁን ሌሎች ልዩነት ሊኖሩ ቢችሉም ኤጀንሲው ዜጎችን እኩል የማስተናገድ ሃላፊነት እንደሚኖረው ገልጸዋል።

ኤጀንሲው ተጠሪነቱ ለኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሆኖ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አጠቃላይ አንቀስቃሴ የሚያቀናጅና የሚያስተባብር የመንግስት ተቋም እንደሚሆንም ነው የተገለጸው።

የኤጀንሲው ዋና ጽህፈት ቤት በአዲስ አበባ የሚከፈት ሲሆን፥ እንዳስፈላጊነቱ በየደረጃው እስከታችኛው የመንግስት መዋቅር ድረስ አደረጃጀት ሊኖረው እንደሚችል ቃል አቀባዩ ጠቁመዋል።

ከዚህም ሌላ ፓርላማ አየቀረበ ሪፖርት የሚያቀርብ አስተያየትና መሻሻያዎችን የሚቀበል የአሰራር ስርዓት እንደሚኖረው ነው የተገለጸው።

ኢትዮጵያውያንን የሚወክሉ ተቋማት ባሉበት አካባቢዎች ሁሉ ያልተገደበ አገልግሎት እንደሚሰጥም ተመላክቷል።(ኤፍ.ቢ.ሲ)