የኦህዴድ ማእከላዊ ኮሚቴ ሲያካሂድ የነበረውን መደበኛ ስብሰባ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ አጠናቀቀ

የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት /ኦህዴድ/ ማእካለዊ ኮሚቴ ለሁለት ቀናት ሲያካሂድ የነበረውን መደበኛ ስብሰባ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ በትናንትናው እለት አጠናቋል።

የኦህዴድ ማእከላዊ ጽህፈት ቤት ሀላፊ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የማእከላዊ ኮሚቴ ስብሰባውን መጠናቀቅ አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፥ 9ኛው የኦህዴድ ድርጅታዊ ጉባዔ ከመስከረም 8 እስከ 10 2011 ዓ.ም እንደሚካሄድ መወሰኑን አስታውቀዋል።

9ኛው የኦህዴድ ድርጅታዊ ጉባዔ “አሸናፊ ሀሳብ ለተሻለ ድል” በሚል መሪ ቃል በጅማ ከተማ እንደሚካሄድም ወይዘሮ አዳነች ተናግረዋል።

ወይዘሮ አዳነች አክልወም፥ ላለፉት ሁለት ቀናት ሲካሄድ የነበረው የኦህዴድ ማእከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ለ9ኛው ድርጅታዊ ጉባዔ ግብአት የሚሆኑ ውሳኔዎችን በማሳለፍ መጠናቀቁንም ገልፀዋል።

የኦህዴድ ማእከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ከዚህ በተጨማሪም የድርጅቱን የ2011 በጀት እቅድን ተመልክቶ ያፀደቀ ሲሆን፥ የተለያዩ ክልላዊ እና ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ በመወያየት አቅጣጫዎችን እና ውሳኔዎችን ማሳለፉን አስታውቀዋል።

ማእከላዊ ኮሚቴው በስብሰባው ማጠቃለያ ላይም የድርጅቱ የትግል ደረጃ፣ የኦሮሞን ባህል እና ወግ መሰረት በማድረግ የኦህዴድን ስያሜ፣ ሎጎ፣ መዝሙር እንዲሁም የመተዳደሪያ ደንብን ለመለወጥ በቀረበው ረቂቅ የውሳኔ ሀሳብ ላይ በመወያየት በድርጅታዊ ጉባዔው ለውሳኔ እንዲቀርብ አቅጣጫ ማስቀመጡንም ተናግረዋል።

ወይዘሮ አዳነኝ አክለውም፥ 9ኛው የኦህዴድ ድርጅታዊ ጉባዔ የኦሮሞ ህዝብ ትግል ወሳኝ ምእራፍ ላይ በደረሰበት ወቅት የሚያካሄድ በመሆኑ ታሪካዊ ያደርገዋል ሲሉም ተናግረዋል።

ጉባዔው ዴሞክራሲያዊ፣ የህዝቡን ጥያቄ እና ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ታሪካዊ ውሳኔዎች የሚተላለፉበት ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅም አንስተዋል።

ኦህዴድ የኦሮሞን ህዝብ ትግል በመምራት ለድል ያበቃ ድርጅት ነው ያሉት ወይዘሮ አዳነች፤ አሁን የተገኘው ድል ሳይሸራረፍ እንዲቀጥል ለማድረግና የበለጡ ድሎችን ለማስመዝገብ ዝግጁ መሆኑንም ገልፀዋል።

የተገኘውን ለውጥ በብቃት ለመምራትም በኦህዴድ 9ኛው ድርጅታዊ ጉባዔ ላይ የሚሳተፉ አባላት ባላቸው እውቀት፣ ብቃት እና ተቆርቋሪነት ላይ ተመስርቶ በከፍተኛ ትኩረት ሊመረጡ እንደሚገባ ማእከላዊ ኮሚቴው አቅጣጫ ማስቀመጡንም ወይዘሮ አዳነች አስታውቀዋል። (ኤፍ.ቢ.ሲ)