አርበኞች ግንቦት 7 ሰላማዊና ህጋዊ ፓርቲ የሆነው የተጀመረውን ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ለማጠናከር ነው- ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ

አርበኞች ግንቦት 7 ወደ ሰላማዊና ህጋዊ ፓርቲነት የመጣው በሀገሪቱ የተጀመረውን ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ለማጠናከር መሆኑን የድርጅቱ ሊቀ መንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገለፁ።

በዛሬው እለት ወደ ሀገር ለተመለሰው አርበኞች ግንቦት 7 በአዲስ አበባ ከተማ ስታዲየም አቀባበል ተደርጓል።

በአቀባበል ስነ ስርዓቱ ላይም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ፣ የአርበኞች ግንቦት 7 ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ የድርጅቱ ጸሃፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ጨምሮ በርካታ የድርጅቱ አባላት እና አመራሮች ተገኝተዋል።

በአቀባበሉ ላይ የተገኙት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋም፥ ደማቅ አቀባበል ላደረጉላቸው የአዲስ አበባ እና አካባቢው ህዝብ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ፕሮፌሰር ብርሃኑ አክለውም፥ ለዛሬዋ ቀን እንድንበቃ መስዋእትነት ለከፈሉ መላው የሀገሪቱ ህዝብ፤ እንዲሁም መብታችን ይከበር ብለው እጃቸውን ባዶ በሰላማዊ መንገድ ለመብታቸው ታግለው ለተሰው ወጣቶችም ምስጋና አቅርበዋል።

እንዲሁም የህዝቡን ትግል በመረዳት እና ትልቅ ሀላፊነት በመውሰድ በኢህአዴግ ውስጥ የለውጥ ሀይል ለሆኑት እንዲሁም የእርቅና የአንድነት መንፈስ ይዘው ለመጡ አመራሮችም ምስጋና አቅርበዋል።

ፕሮፌሰር ብርሃኑ፥ አሁን በሀገሪቱ የተጀመረው የለውጥ ሂደት ሀገሪቱን እውነተኛ ዴሞክራሲያዊት ከመሆን ውጭ ሌላ መደራሻ የለውም ሲሉም ተናግረዋል።

አርበኞች ግንቦት 7 ወደ ሀገር ቤት በመመለስ ሰላማዊ እና ህጋዊ ፓርቲ ለመሆን የወሰነውም በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ የተጀመረውን ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ለማጠናከር እንደሆነም ገልፀዋል።

“በቀጣይ ሁላችንም ቂምና በቀል አርቀን፤ ሁላችንም ተጋገዘን ሀገራችንን ወደ ተሻለች ደረጃ እንውሰዳት” ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

ለፖለቲካ ፓርቲዎች ባስተላለፉት መልእክት፥ በአመለካከት ከምንስማማቸው ጋር እየተዋሃድን ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲ መፍጠር ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

በአቀባበል ስነ ስርዓት ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ፥ አመራሮቹ እና አባላቶቹን እንኳን በሰላም ወደ ሀገራችሁ መጣችሁ ብለዋል።

በመላው ሀገሪቱ እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ የለውጥ ስራዎች እየተሰሩ ባለበት ወቅት እነ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው ለውጡን የበለጠ ለማስቀጠል ይረዳል ሲሉም ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በከተማ አስተዳደሩ ሰፋፊ የለውጥ ስራዎች እየተሰሩ ነው ያሉት ኢንጂነር ታከለ ኡማ፥ በምንሰራው ስራ የሚያግዙን ከሆነ ዝግጁ ነን ሲሉም ተናግረዋል።

ኢንጂነር ታከለ፤ በመካከላችን ያለው ግንብ ፈርሷል ያሉ ሲሆን፥ አሁን አንድ ሆነን ከተማችን እና ሀገራችንን በጋራ እንገንባ ሲሉም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

የአርበኞች ግንቦት 7 ዋና ፀሃፊ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ በበኩላቸው፥ በተደረገላቸው አቀባበል መደሰታቸውን ገልፀው፤ ይህንን ያስተተባበረውን አካል አመስግነዋል።

አቶ አንዳርጋቸው አክለውም፥ ኢትዮጵያ የወጣቱ የስራ አጥነት ችግር እስኪቀረብ እና ሁሉም ተደላድሎ የሚኖርባት ሀገር እስክትሆን ድረስ ትግላችን ይቀጥላል ብለዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሚመራውን መንግስት ጨምሮ ለህዝቡ ለውጥ ከሚታገሉት አካላት ጋር በሙሉ በትብብር እንሰራለን ሲሉም ተናግረዋል።(ኤፍቢሲ)