ተመድ በኢትዮጵያ አማካኝነት በጅቡቲና በኤርትራ መካከል የተደረሰውን ስምምነት አደነቀ

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በኢትዮጵያ አማካኝነት በጅቡቲ እና በኤርትራ መካከል የተደረሰውን ስምምነት አድነቀዋል፡፡

ዋና ጸሃፊው ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ሶማሊያ እና ጅቡቲ በቀጠናው ሰላም እና መረጋጋት ለማስፈን እንዲቻል የደረሱበት የጋራ ስምምነት ለምስራቅ አፍሪካ እና ለሌሎች አገሮች ምሳሌ የሚሆን ነው ብለዋል።

ጉቴሬዝ አያይዘውም ሀገራቱ አሁን እያስገኙ ያሉትን በጎ ጅምሮች እንዲጠናከሩ ለማድረግ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከጎናቸው መሆኑን ገልጸዋል።

በቅርቡ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከሶማሊያው ፕሬዚዳንት ጋር ወደ ኤርትራ በሄዱበት ወቅት በጅቡቲ እና በኤርትራ መካከል የተፈጠሩት ችግሮች መፈታት እንዳለባቸው ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር የጋራ መግባባት ላይ መድረሳቸው አይዘነጋም።

ይህንን ተከትሎ የኢትዮጵያ፣ የኤርትራ እና የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በጅቡቲ በተገኙበት ወቅት ፕሬዚዳንት ኦማር ጊሌ የኢትዮጵያ መንግስት ከኤርትራ ጋር ያለውን ችግሮቻችንን እንድንፈታ እያደረገ ላለው አስተዋጽኦ ማመስገናቸው ይታወሳል።(ምንጭ: የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት)