የአማራ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝና የጋምቤላ ክልሎች ከ3 ሺህ 550 በላይ ለሚሆኑ የህግ ታራሚዎች ይቅርታ አደረጉ

የአማራ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና የጋምቤላ ክልሎች ከ3 ሺህ 550 በላይ ለሚሆኑ የህግ ታራሚዎች ይቅርታ ማድረጋቸውን አስታወቁ።

የአማራ ክልል ፍትህ ቢሮ ሀላፊ አቶ ፍርዴ ቸሩ እንደተናገሩት፥ የክልሉ መንግስት ለህግ ታራሚዎቹ ይቅርታውን ያደረገው የ2011 አዲስ ዓመትን አስመልክቶ ነው።

ለህግ ታራሚዎቹ ይቅርታ የተደረገውም የአማራ ክልል ፍትህ ቢሮ የይቅርታ ቦርድ ከ3 ሺህ በላይ ታራሚዎቹ ይቅርታ ተደርጎላቸው እንዲፈቱ ያቀረበውን ጥያቄ ተከትሎ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ይቅርታ የተደረገላቸው የሀግ ታራሚዎችም ከዛሬ ማለዳ ጀምሮ ከማረሚያ ቤቶች እየወጡ ቤተሰቦቻቸውን መቀላቀል መጀመራቸውንም አቶ ፍርዴ አስረድተዋል።

በተመሳሳይ የጋምቤላ ክልል የማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ሀላፊ ኮሚሽነር ቲቶ ሀዋርያ  እንደተናገሩት፥ በክልሉ የተለያዩ ወንጀሎችን በመስራት ተፈርዶባቸው የነበሩ ከ370 በላይ ታራሚዎች ከእስር እንዲፈቱ ተደርጓል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ሀላፊ ኮሚሽነር አዲሱ ሀተሴም በክልሉ የተለያዩ ወንጀሎችን ሰርተው ተፈርዶባቸው የነበሩ 188 ታራሚዎች በይቅርታ መፈታታቸውን አስታውቀዋል።

ከእነዚህ ውስጥም ዘጠኙ ሴት ታራሚዎች መሆናቸውን ኮሚሽነር አዲሱ ተናግረዋል።(ኤፍ.ቢ.ሲ)