በወጣቶች መካከል እየተፈጠረ ያለውን ግጭትና ህገ ወጥ ተግባር ከዚህ በኋላ እንደማይታገስ የፌደራል ፖሊስ አስታወቀ

ወደ ሀገር ቤት የሚገቡ የድርጅት አመራሮችን ለመቀበል በሚደረግ ቅድመ ዝግጅት ላይ በወጣቶች መካከል እየተፈጠረ ያለውን ግጭትና ህገወጥ ተግባር ከዚህ በኋላ እንደማይትገስ የፌደራል ፖሊስ አስታወቀ።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ዘይኑ ጀማል ከአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር የስራ አስፈጻሚ አባል አቶ ኢብሳ ነገዎ ጋር በመሆን መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫው ላይም ኮሚሽነር ጀነራል ዘይኑ ጀማል፥ በትናንትናው እለት እና ዛሬ ወደ ሀገር ቤት የሚገቡ የድርጅት አመራሮችን ለመቀበል በሚደረግ ቅድመ ዝግጅት ላይ በወጣቶች መካከል ግጭት መፈጠሩን አስታውቀዋል።

በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራውን የኦነግ ቡድን ለመቀበል እየተደረገ ባለ ቅድመ ዝግጅት ወቅት ወጣቶች የድርጅቱን አርማ ለመስቀል ዝግጅት እያደረጉ ነበር፤ ይህንን የከለከላቸው አካል የለም ያሉት ኮሚሽነር ዘይኑ፥ ሆኖም ግን አስፋልትን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማትን እንዳያቀልሙ ተከልክው፤ ይህንንም ተወያይተን እሺ ብለው ተቀብለው ትተው ነበር ብለዋል።

ሆኖም ግን ማንም ያልፈቀደላቸው አካላት የእነሱን ባንዲራ አውርደው የሌላን ለመስቀል ሲሉ ግጭት ተፈጥሯል ሲሉም ገልፀዋል።

ግጭቱ ለማንም ጠቃሚ አይደለም ያሉት ኮሚሽነር ጀነራል ዘይኑ፥ ችግሩን በውይይት መፍታት ሲቻል ወደ አላስፈላጊ ግጭት መግባት ተገቢ አይደለም ሲሉም ተናግረዋል።

ፖሊስ የህግ የበላይነትን የማስከበር ሀላፊነት ስላለበት ከዚህ በኋላ እንዲህ አይነት ግጭቶችን በትእግስት እንደማያልፍም ኮሚሽነር ዘይኑ አሳስበዋል።

የአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፥ የዴሞክራሲ ስርዓትን እንገንባ ብለን ስንነሳና ስርዓቱን ለመገንባት የሚያስፈልግ እነዚህን ባህሪያትን ተቀብለን ካልተነሳን ግን ስርዓቱን መገንባት አንችልም ብለዋል።

የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ውስጥ ልዩነቶችን መቀበል የግድ ነው ያሉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፥ ልዩነቶቹ ደግሞ ሀሳቦችን፣ አርማዎችን እና ባንዲራዎችን ሊያጠቃልል ይችላል ብለዋል።

ትናንትና እና ዛሬ በአዲስ አበባ የተስተዋሉ ችግሮች ደግሞ ከዚህ ጋር የሚፃረሩ ነው ያሉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፥ ማንኛውም አካል ስሜቴን ይገልፅልኛል ያለውን አርማ የመያዝ እና የማውለብለብ መብት አለው ሲሉም ተናግረዋል።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር የስራ አስፈጻሚ አባል አቶ ኢብሳ ነገዎ በበኩላቸው፥ ሰሞኑን በአዲስ አበባ እና አካባቢዋ የተስተዋለው ችግር ተቀባይነት የሌለው መሆኑን አንስተዋል።

ወጣቱም ከዚህ አይነት እንቅስቃሴዎች ሊቆጠብ እንደሚገባም አቶ ኢብሳ ጥሪ አስተላልፈዋል።

አሁን ላይ እየታየ ያለው ግጭት እና ያልተገባ ፉክክር ድርጅታቸውን የማይወክል መሆኑንም ነው አቶ ኢብሳ የተናገሩት።(ኤፍ.ቢ.ሲ)