ኢትዮጵያና ኤርትራ ይፋዊ የሰላም ስምምነት በጅዳ ይፈራረማሉ

ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በቅርቡ የገቧቸውን የሰላም ስምምነቶች የሚያጠናክር ስምምነት ነገ በሳዑዲ አረቢያ በሚካሄድ ስነ ስርዓት ይፈራረማሉ።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቃል አቀባይን ጠቅሰው የተለያዩ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡትም በሪያድ በሚካሄደው የፊርማ ስነ ስርዓት ላይ የተመድ ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ እና የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ  ፋቂ እንዲሁም የሳዑዲ አረቢያው ንጉስ ሳልማን ይገኛሉ ተብሏል።

በቅርቡ ግኑኝነታቸውን ያደሱት ሁለቱ ሀገራት አስመራ ላይ በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጉብኝት ወቅት የሰላምና የወዳጅነት ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል።

ያንንም ተከትሎ በሀገራቱ መካከል የአየር ትራንስፖርት ተጀምሯል፤ ሁለቱም አገራት ኤምባሲዎቻቸውን ከፍተዋል፤ በዚሁ ሳምንትም ሁለቱ ሀገራት ዝግ ሆነ የቆየውን ድንበራቸውን ክፍት በማድረግ በየብስ ትራንስፖረት መገናኘት ጀምረዋል።