ኢትዮጵያና ኤርትራ አለመግባባታቸውን ለመፍታት ያሳዩትን ቁርጠኝነት የሳዑዲ መንግስት አደነቀ

ኢትዮጵያና ኤርትራ ለሃያ ዓመት የዘለቀውን አለመግባበት በሰላም ለመፍታት ላሳዩት ቁርጠኝነትና አመራር የሳዑዲ መንግስት እድናቆቱን መግለጹን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ፍጹም አረጋ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ኢትዮጵያ ከኤርትራና ከሳዑዲ አረቢያ ጋር ለምታደርገው የሦስትዮሽ ስብሰባ ለመሳተፍ ወደ ጂዳ ሳዑዲ አረቢያ ማቅናታቸው ይታወቃል።

በዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ፥ በወደብ ልማት፣ በቱሪዝም፣ በሆስፒታል ልማት እንዲሁም በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ ትብብራቸውን ለማጠናከር በሚችሉበት አግባብ ውይይቱን መጀመራቸውን አቶ ፍጹም በማህበራዊ ድረ ገጻቸው አስፍረዋል።

በሳዑዲ ቆይታቸው በሦስቱ አገራት ስለሚኖረው የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብር ዙሪያ እንደሚወያዩ ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ስለተደረገው የሰላም ስምምነትና ይህንን ተከትሎ በተፈጠረው መልካም የኢንቨስትመንት ዕድል ከሳዑዲው ንጉስ ሳልማንና ከአልጋ ወራሽ ሙሐመድ ቢን ሳልማን ጋርም ይመክራሉ ሲሉም አቶ ፍጹም አረጋ አስረድተዋል፡፡

የሰላም ስምምነቱ በሁለቱ አገራት የሚኖረውን ወንድማማች ሕዝብ ለዘመናት በጋራ ያቆየውን ታሪክ፣ ባህል፣ ቋንቋና ጉርብትና በተጠናከረ መልኩ እንዲቀጥል የሚያስችል መሆኑም ነው የተገለጸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በፈረንጆቹ ሃምሌ 24፣ 2018 ላይ በተመሳሳይ መልኩ የልዑካን ቡድን መርተው ወደ ተባበሩት ዓረብ ኢሜሬትስ በማቅናት በኢትዮጵያና በኤርትራ መንግስት መካከል በተፈጠረው ሰላም ኢትዮጵያ ከተባበሩት ዐረብ ኢሜሬትስና ከኤርትራ መንግስት ጋር በመሆን በወደብ ልማት፣ በመሰረተ ልማትና በአጠቃላይ በሎጂስቲክስ ሊኖራቸው ስለሚችለው የኢንቨስትመንት ትብብር ውይይት ማድረጋቸው የሚታወስ ነው፡፡ (ኤፍ.ቢ.ሲ)