ኢህአዴግ ምክር ቤት ስብሰባ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ተጠናቀቀ

ከመስከረም 04-05/2011ዓ.ም ሲካሂድ የቆየው የኢህአዴግ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ተጠናቋል።

የኢህአዴግ ምክር ቤት ከመስከረም 4 እስከ 5 ቀን 2011 ዓ.ም ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታና ለውጡን በብቃት የመምራት አስፈላጊነት ዙሪያ እና በ11ኛው ድርጅታዊ ጉባዔ ረቂቅ ሪፖርት ላይ ተወያይቷል፡፡

የኢህአዴግ ም/ቤት በመጋቢት ወር ባካሄደው ስብሰባ ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች እና ያካሄደውን የአመራር ለውጥ ተከትሎ የተወሰዱ የለውጥ እርምጃዎች ህዝባዊ፣ ህገ-መንግስታዊ እና ኢህአዴጋዊ መሆናቸውን አረጋግጧል፡፡

በፖለቲካው መስክ ፖለቲካዊ መረጋጋት ለማምጣት ፣ የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት እና ሰብአዊ መብቶች ለማስከበር የተወሰዱ እርምጃዎች፣ በዲፕሎማሲው መስክ የተገኙ ውጤቶች በተለይም የኤርትራና የኢትዮጵያ ህዝቦችን ደም አቃብቶ የነበረው ጦርነት የፈጠረውን ለሁለት አስርተ ዓመታት የዘለቀው ፍጥጫ በመቅረፍ ወትሮውንም መኖር ይገባው ወደነበረ ቤተሰባዊነት በአጭር ጊዜ ውስጥ መመለስ የተቻለ መሆኑ ጉልህ ስፍራ የሚሰጠው መሆኑን እና ይህም ከጎረቤት ሀገራት ጋር የተሳሰረ ህልውና ያለን መሆኑን ግምት ውስጥ ያስገባ ሚናችንን በአግባቡ የምንወጣበት ዕድል እየተፈጠረ መምጣቱ፣በማህበራዊ መስክ በኢትዮጵያ ተዋህዶ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ውስጥ እና በእስልምና እምነት ተከታዮች መካከል አንድነትን ለማጠናከር የተከናወኑ ተግባራት ዉጤት እንዳመጡ ገምግሟል፡፡

በተጨማሪም ሀገራዊ መግባባት ለማምጣት የተደረጉ ጥረቶች በተለይም በሀገራችን የተለያዩ የፖለቲካ አቋሞችን ይዞ ነገር ግን ከመጠፋፋት በመለስ ጎን ለጎን የሁሉም አለቃ ለሆነው ህዝብ በነፃነትና በሰላማዊ መንገድ ለመቅረብ የሚችሉበት የፖለቲካ ምህዳር ለመፍጠር የተጀመረው ጥረት በሀገራችን አዲስ ምዕራፍ ለመጀመር መሰረት የጣለ መሆኑን፣ ለበርካታ አስርተ ዓመታት ባለመግባባት የሚታወቀውን የመንግስትና የዲያስፖራ ግንኙነት ወደ አወንታዊ ተደማሪነት በሚቀይር አግባብ ለመምራት የተደረገው ጥረት፣ እና በኢኮኖሚው መስክ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለማቃለል፣ የዋጋ ንረትን ለመግታት፣ ህገ-ወጥ ንግድን እና የገንዘብ ዝውውርን ለመቆጣጠር እንዲሁም ንግድ እና ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት የተሰሩ ሥራዎች ውጤታማ እንደሆኑ በመገምገም፤ ወደፊትም ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እና መዋቅራዊ ችግሮቹን በሂደት ለመፍታት በሚያስችል አግባብ እንዲፈፀም አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

ምክር ቤቱ ከላይ እየተመዘገቡ ያሉ ዉጤቶችን ቀጣይነት እና ዘላቂነት የሚፈታተኑና መሰረታዊ የሆኑ ሊፈቱ የሚገባቸዉ  ችግሮች እንዳሉም አፅንኦት ሰጥቶ መክሯል፡፡ በዚህ ረገድ የሚጠቀሱት በወጪ ንግድ መስክ በሚታየዉ የአፈፃፀም ዝቅ ማለት ምክኒያት የውጭ ምንዛሪ እጥረት መኖሩ፣ የውጭ ብድር የመክፈል አቅማችን እየተዳከመ መምጣት፣ የገቢ አሰባሰባችን ዝቅተኛ ሆኖ መቆየት እና የኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር ዕጦት ችግሮችን ለመቅረፍ የተጀመሩትን የሪፎርም ሥራዎች በፍጥነት በማሻሻል በተጠያቂነት አግባብ ለመፈፀም ከፍተኛ ርብርብ መደረግ እንዳለበት በጥልቀት ተወያይቷል፡፡  የውጭ ምንዛሪ እጥረታችንን ለመቅረፍም ሆነ የዜጎችን ተጠቃሚነት በማሳደግ ሀገራዊ ዕድገቱን ለማስቀጠል የምርትና ምርታማነትን በቀጣይነት ማሻሻል፣ በኢንዱስትሪው ዘርፍም ይሁን በግብርናው መስክ የተጀመሩትን አጠናክሮ ከመፈፀም ባሻገር መሻሻል የሚፈልጉን በተከታታይ እየለዩ ማሻሻል በሚቻልባቸው አቅጣጫዎች ዙሪያ ሰፋ ያለ ውይይት በማካሄድ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ እንዲሁም የዲሞክራሲ ተቋማትን ለማጠናከር፣ የፌደራል ሥርዓታችን ብሔረሰባዊና ኢትዮጵያዊ ማንነትን አስማምቶ በመሄድ ረገድ የሚያጋጥሙ የአመለካከትም ይሁን መዋቅራዊ ችግሮችን መቅረፍ እንደሚገባ እና ለዚህም ተከታታይ የለዉጥ እርምጃዎች እንዲወሰዱ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

የግንባሩ ምክር ቤት ህዝቡ የታገለዉ መሰራታዊ ጥቅሞቹ ፣ ሰብአዊ እና ዴክራሲያዊ መብቶቹ እንዲረጋገጡለት እንጂ ስርአት አልበኝነት እንዲመጣ እንዳልሆነ በማስመር ምልአተ ህዝቡ የህግ የበላይነት እንዲከበር በፅናት እንዲታገል እና ለዉጡን ጠብቆ እንዲያስቀጥል ጥሪዉን አቅርቧል፡፡

ም/ቤቱ ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታና ለውጡን በብቃት የመምራት አስፈላጊነትን አስመልክቶ ባደረገው ውይይት የለውጡን ገፊ ምክንያቶች በመመርመር የተጀመረው ለውጥ ማዕከሉ ዘላቂ ተቋማዊ ብቃት መገንባት ሊሆን እንደሚገባዉ አስምሮ፤ ለውጡ ተቋማዊና ህጋዊ ማዕቀፍ ይዞ ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

በዚህም መሰረት የፖለቲካ ሪፎርሞች በሶስት ዘርፎች ማለትም የኢህአዴግ የውስጠ ድርጅት ሪፎርም፣ አስተዳደራዊ ሪፎርም እና የህግ ሪፎርም የማካሄድ አስፈላጊነት ላይ ስምምነት ተደርሷል፡፡ በዚህ ላይ ተመስርቶ የድርጅቱን ተራማጅነት፣ ውስጣዊ አንድነት፣ አንፃራዊ ነፃነት እና የአሰራር ምቹነት ለማጎልበት ሊሰራ እንደሚገባ፤ ጠንካራ እና መልካም የመንግስት አስተዳደር ለመፍጠር ያልተማከለና ለዘርፍ ልዩ ባህሪ ትኩረት የሚሰጥ ሪፎርም ማድረግ እንደሚያስፈልግ፤ የፍትህ ተቋማት፣ የምርጫ ቦርድ እና የደህንነት ተቋማትን ነፃና ገለልተኛ ለማድረግ የሚያስችል ሪፎርም እንዲካሄድ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

የኢህአዴግ ምክር ቤት እመርታዊ ለውጥ እና መለያ መርሆዎቹን በተመለከተ የመደመር ፅንሰ ሀሳብ ላይ በመምከር ጽንሰ ሀሳቡ ከድርጅቱ መርሆዎችና እሴቶች ጋር የተጣጣመ ይልቁንም ሀገራዊ ይዘትና ፋይዳ ያለው የሰላም፣ የፍቅር እና የይቅርታ እሳቤ መሆኑን በማመን ፅንሰ ሀሳቡ እንዲበለፅግ፣ ህዝቡ በሙሉ ፍላጎቱ እንዲያውቀው፣ እንዲያሰፋው ብሎም የለውጥ መርሆዎቹን ተገንዝቦ በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ተሳትፎ እንዲያደርግ የሚያስችል ሥራ መስራት እንደሚያስፈልግ፣ አባላትም በቂ ግንዛቤ እና የተሟላ እውቀት ጨብጠው ፅንሰ ሀሳቡን ማስፋት የሚችሉበት ቁመና እንዲይዙ ሊሰራ እንደሚገባው ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

ምክር ቤቱ የግንባሩ 10ኛው ጉባዔ በድርጅትና በመንግስት ሥራዎች መስክ ያስቀመጣቸውን አቅጣጫዎች ሪፖርት የገመገመ ሲሆን ‹‹ሀገራዊ አንድነት፣ ለሁለንተናዊ ለውጥ!›› በሚል መሪ ቃል በመጪው መስከረም መጨረሻ ለሚካሄደው አስራ አንደኛው ጉባዔ የሚቀርቡ አቅጣጫዎች ላይም መክሯል፡፡ ምክር ቤቱ በሁለት ቀን ውሎው መጪው 11ኛ ጉባዔ በሀገራችን ህልውና ላይ አንዣቦ ለነበረው አደጋ መነሻ የነበሩና በየደረጃው ተከስተው የነበሩ ድክመቶችን ለማረም ወሳኝ የለውጥ ሂደት በጀመርንበትና አዲስ ህዝባዊ መነቃቃትና ተስፋ መፈንጠቅ በጀመረበት ወቅት የሚካሄድ መሆኑን በማረጋገጥ ለውጡን በብቃት ለመምራት በሚያስችሉ የድርጅትና የመንግስት ሪፎርም ጉዳዮች ዙሪያ በስፋት ተወያይቶ ውሳኔዎች አሳልፏል፡፡

ምክር ቤቱ በዚሁ ስብሰባ የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የግማሽ ዘመን አፈፃፀም በመገምገም የቀሪውን ጊዜ የትኩረት አቅጣጫዎች በማስቀመጥ በሀገሪቱ የተጀመረውን ቀጣይነት ያለው ዕድገት አጠናክሮ በማስቀጠል የህዝባችንን ተጠቃሚነትና የኢትዮጵያችንን ብልፅግና ማፋጠን የሚያስችሉ ውሳኔዎች የሚተላለፉበት በመሆኑ ለዚሁ መነሻነት በድርጅትና ፖለቲካ፣ በዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ፣ በለውጥና መልካም አስተዳደር እንዲሁም በኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት መስክ የተቀመጡትን የቀጣይ ዓመታት አቅጣጫዎችን በዝርዝር ፈትሾ በማዳበር አፅድቋል፡፡

የኢህአዴግ ም/ቤት በአጠቃላይ የተጀመረው ለውጥ ገና ከወዲሁ እያስመዘገበ ያለው ውጤት ይበል የሚያሰኝ መሆኑን በማስመር ለውጡ ተቋማዊ እና ቀጣይነት ያለው እንዲሆን ይበልጥ መስራት እንደሚገባ አስቀምጧል፡፡ 11ኛው ድርጅታዊ ጉባዔም በስኬት እንዲጠናቀቅ የቀሪ ጊዚያት የዝግጅት ሥራዎች እንዲጠናቀቁ አቅጣጫ በማስቀመጥ፣ ሃዋሳ የምታስተናግደው 11ኛው የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባኤ ከመስከረም 23 እስከ 25 ቀን 2011ዓ.ም እንዲካሄድ ወስኗል፡፡

ምክር ቤቱ ለለውጡ ቀጣይነት እና ለጉባዔው ስኬት መላው የድርጅቱ አመራር፣ አባላት እና ህዝቡ የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ እና የዘወትር ድጋፋቸውን እንዲሰጡ ጥሪውን በማቅረብ መደበኛ ስብሰባውን አጠናቋል፡፡

በመጨረሻም የኢህአዴግ ም/ቤት ለመላው ኢትዮጵያውያን 2011ዓ.ም የሰላም፣ የይቅርታ፣የፍቅር እና የአንድነት እንዲሆን መልካም ምኞቱን ገልጿል፡፡